ህወሃትን መደገፍ ወንጀል ነው- አገው ብሔራዊ ሸንጎ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመውን የህወሓት ቡድን መደገፍ ወንጀል ነው ሲል የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ኮነነ።

መንግስት በህወሓት ላይ የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲያጠናክር፤ ሕወሐትም በድርጊቱ ተጸጽቶ ምህረት ሊጠይቅ እንደሚገባው ገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ አመራሮች የህወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት እጅጉን እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው ፓርቲያቸው ከተመሰረተ ጀምሮ ህወሓት ከቀደመ የጥፋትና የሴራ ፖለቲካ ታሪኩ ይፈወሳል በሚል የአገው ህዝብም በትግራይ ስለሚኖር ቅርበት እንደነበረው ይናገራሉ።

ዳሩ ግን ቡድኑ ከሰሞኑ አገርንም በሚጠብቅ፣ የክልሉን መንግስት አምኖ በተቀመጠበት የፈጸመበት ጥቃት ፈጽሞ ከወታደራዊ ህግ ያፈነገጠ፣ ኢትዮጵያዊያንን ያሳዘነ ድርጊት ብለውታል።

ህወሓት ትግል ላይ በነበረበትም ሰዓት ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ ለነጻነት የሚታገሉ የኢህአፓ ታጋዮችን በተኙበት በጅምላ እንደረሸናቸው አስታውሰዋል።

አሁንም ህወሓት መንግስት ሆኖ በሚመራው ክልል አገር ዳር ድንበር የሚከላከል ሰራዊት መንግስትን አምኖ በተቀመጠ ሰራዊት ጥቃት በመፈጸም በኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ክህደት መፈጸሙን ገልጸዋል።

የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ መስፍንና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው፣ አቶ ገብረሕይወት መላውም ህወሓት የፈጸመው ድርጊት ፓርቲውን እንዳሳዘነው ጠቅሰዋል።

ድርጊቱ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ ፓርቲው እንዳወገዘው አስታውቀዋል።

ሸንጎው ህወሓት ከራሱ ውጭ ለማንም እንደማይሆን ያረጋገጠበት፣ ጥቃቱም ልጇን እንዳረደች እናት ይቆጥረዋል ብለዋል አመራሮቹ።

አቶ አላምረው ይርዳው የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ዋጋ የከፈለ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የህወሃት ቡድንን መደገፍ ወንጀል መሆኑን ገልጸው፤ ህወሃት የትግራይ ህዝብን፤ አገርን ነው የከዳው ብለዋል።

በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት ቡድኑ ለማንም የማይመለስ ለእራሱ ብቻ የቆመ መሆኑን ነው ያሳየ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ወጣት ፈቃዱ መስፍን በአንድ አገር ሁለት መንግስት አይኖርም፤ የዜጎችን ሰላም ደህንነት ለመጠበቅ ብሎም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዳይፈርስ ለመከላከል ህግ ማስከበር የመንግስት ግዴታ መሆኑን አንስቷል።

“ሰራዊታችን እኛን አገርን ሊጠብቅ እስከቆመ ድረስ መንግሰታዊ በሆነ እራሳቸው በመሰረቱት ተቋም ላይ ጥቃት ማድረሱ አስነዋሪ ነው” ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አቶ ገብረሕይወት ሙላው ናቸው።

ሸንጎው ይህ ድርጊት ዳግመኛ እንዳይደገም ተደርጎ መስተካከል አለበት የሚል አቋም ይዟል ብለዋል።

መንግስት ሕግ ለማስከበር የወሰናቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በጊዜያዊ መንግስት የማቋቋምና የሕግ ማስከበር እርምጃዎች የሚደገፉ መሆናቸውን አመራሮቹ ገልጸው፣ህግ ማስከበር ስራውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በተለይም በክልሉ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አካል መንግስት በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ተናግረዋል።

መንግስት በሕግ በማስከበር ሂደትም ንጹሃን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ማድረግና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አሳፋሪ ድርጊት የፈፀመው ህወሓት ቡድን የክልሉን መንግስትነትም ለፌዴራል መንግስት በማስረከብ ከስህተቱ ተምሮ ምህረት ሊጠይቅ እንደሚገባው አክለዋል።

"ህወሓትን መደገፍ ወንጀል ነው" ነው ያለው ፓርቲው፤ ከህወሓት ጎን ሆነው ለጦርነት የሚገፋፉ አካላት ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

ትግራይ ሕዝብም ስጋት ሳይገባው ከኢትዮጵያውያን ጎን ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም