ኢትዮጵያ የ2021 ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙንኬሽን ልማት ኮንፍረንስን አዘጋጅ አገር ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የ2021 ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙንኬሽን ልማት ኮንፍረንስን አዘጋጅ አገር ሆነች
ኢትዮጵያ የ2021 የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙንኬሽን ልማት ኮንፍረንስ አዘጋጅ አገር መሆኗን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ጋር በበይነ -መረብ አማካኝነት በኢትዮጵያ ሊካሄድ በታሰበው ''ወደ አዲስ ጉዞ'' ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙንኬኝን ልማት ኮንፍረንስ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በእለቱ በኢትዮጵያ መንግስት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፉ ቴሌኮሙንኬሽን ህብረት መካከል የዝግጅቱን አፈጻጸምን የተመለከተ ስምምነት ተደርጓል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ መረሃ ግብሩን አስመልክቶ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና አይሲቲ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።
በመንግስት በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል አንዱና መሰረታዊዩ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አላቸው ተብሎ ከተለዩት ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂና አይሲቲ አንዱ ሆኖ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳና በአስር አመቱ የመሪ ልማት እቅድ ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቷ ይህን መረሃ ግብር እንድታካሄድ እስችሏታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ለመጀመሪያ የ2021 አዘጋጅ አገር በመሆኗ ከመላው አፍሪካ ጋር በአይሲቲና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለትብብር አስቻይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመስራት መዘጋጀቷን ገልጸዋል።
ለመረሃ-ግብሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አንድ ብሄራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላ በኢትዮጵያ ሚካሄደው ኮንፍረንስ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አክለዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታደርገው የላቀ ተሳትፎ በተለይ የቱሪዝም ዘርፉን ከመደገፍ አኳያ ላቅ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።
ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙንኬሽን ልማት ኮንፍረንስ ከዓለም የተውጣጡ 2 ሺህ 500 የሚሆኑ በዘርፍ የሚሰሩ አካለት የሚሳተፉበት ይሆናል።
መረሃ ግብሩ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2021 እንዲሁም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።