ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ታግሎ በማሸነፍ ነጻነቱን ማወጅ አለበት--- በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ከመከላከያ ኃይል ጎን በመሰለፍ ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ታግሎ ነጻነቱን ማወጅ እንዳለበት በአዲስ አበባ የሚኖሩ የተግራይ ተወላጆች ተናገሩ። 

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ብልጽግና ፓርቲ አባላት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።    

በውይይቱም በአገር መከለከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በፌዴራል መንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ባለመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት ልክ ከአገራዊ ለውጡ እየተጠቀመ አለመሆኑን ያነሱት ተወያዮቹ፣ ይህም የሆነው በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማራው የህወሓት ቡድን እንቅፋት በመሆኑ ነው ብለዋል።  

የትግራይ ህዝብ ነጻነቱን ማወጅ ያለበት ወቅት ላይ መሆኑን የገለጹት ተወያዮቹ፣ ለዚህ ደግሞ ከመከላከያ ጎን በመቆም ለነጻነቱ እንዲታገልና አጋርነቱን በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል።   

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ እስከዳር መላኩ የአገር ዳር ድንበርን እየጠበቀ ባለ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም አገር ከመግደል እንደማይተናነስ ገልጸው፣ ይህን ተግባር በአንድነት ማውገዝ እንደሚገባ አጽንኦት ገልጸዋል።   

"አሁን ላለንበት ደረጃ የትግራይ እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን በመገበር ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ይሄ ህዝብ ደግሞ ይህ አይገባውም'' ሲሉም ነው የተደመጡት።

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ከልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሰራበት ጊዜ እንጂ አላስፈላጊ መስዋዕትነትና ቁርሾ ውስጥ የሚገባበት እንዳልሆነም አምልክተዋል።

"የትግራይ ህዝብ በፌዴራል መንግሥት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ጥቂት ቡድኖች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን በመረዳት ለአገር መከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ሊያደረግ ይገባል" ብለዋል ወይዘሮ እስከዳር።

የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ተካ አባይ በበኩላቸው፣ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ሰላማቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

የጭቆና ሥርዓቱን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ሠላማዊ ዜጎችን በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ህወሓት እየሰራ ያለው ሥራ የትግራይ ህዝብ ለአገር አንድነት የከፈለውን ዋጋ መና የሚያስቀር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ናትናኤል ብርሃኔ ናቸው።

መላው ህዝብ ከትግራይ ተወላጆች ጋር በመሆን ጥበብ በተሞላበት መንገድ በህወሓት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ስኬታማ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም