አየር መንገዱ ያስገባቸው ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖች የገበያ ተወዳዳሪነቱን ይጨምራል - አቶ ተወልደ ገብረማርያም - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ያስገባቸው ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖች የገበያ ተወዳዳሪነቱን ይጨምራል - አቶ ተወልደ ገብረማርያም
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ያስገባቸው ሁለት ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችሉታል” ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናገሩ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ የገቡት አውሮፕላኖች አየር መንገዱ ከዚህ በፊት ከነበረው ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸሩ ዘመናዊና የተሻሉ ናቸው።
"አውሮፕላኖቹ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችሉታል" ብለዋል።
እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ፣ እነዚህ ዘመናዊ አውሮፕላኖች የመንገደኛ መስተንግዶን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሻገር አየር መንገዱን ተመራጭ ያደርጉታል።
ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደሚያግዙም ጠቁመዋል።
"በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘው የአቪዬሽን ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ዳግም እያንሰራራ ስለሆነ ኢትዮጵያ እነዚህን ዘመናዊ አውሮፕላኖች ማስገባቷ የተሻለ እድል ይፈጥራል" ብለዋል።
አየር መንገዱ ያስገባቸው አውሮፕላኖች በአፍሪካ በዘርፉ የተፈጠሩ አዳዲስ እድሎችን ለመጠቀም የጎላ ፋይዳ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ በ2017 ያዘዛቸውን ኤር ባስ ኤ-350 ሁለት አዳዲስ አውሮፕላኖች ባለፈው ቅዳሜ መረከቡ ይታወቃል።