የትግራይን ህዝብ ነጻነት ማቀዳጀት የሚቻለው ህገ-ወጡን የህወሓት ቡድን ከጫንቃው ላይ ማውረድ ሲቻል ነው---የመንግስት ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይን ህዝብ ነጻነት ማቀዳጀት የሚቻለው ህገ-ወጡን የህወሓት ቡድን ከጫንቃው ላይ ማውረድ ሲቻል ነው---የመንግስት ሠራተኞች
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ) የትግራይን ህዝብ እንደሌሎች ህዝቦች ነጻነቱን ማቀዳጀት የሚቻለው ህገ-ወጡን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጫንቃው ላይ ማውረድ ሲቻል መሆኑን በቦሌ ክፍለ ከተማ የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመንግስት ሠራተኞች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱም የመንግስት ሠራተኛው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ሳይረበሽ ህዝባዊ አገልግሎቱን ከምንጊዜውም በላይ በተሻለ መልኩ ማቀላጠፍ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
እያንዳንዱ ሠራተኛ ራሱን ከህገ ወጥ ተግባራት ከማራቅ ባለፈ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲያስተውልም ለሚለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ተነስቷል፡፡
የህወሓት የጥፋት ቡድን የህዝብ ደጀን በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት በመኮነን ሁሉም ዜጋ ከሠራዊቱ ጎን መቆሙን በተግባር ሊያረጋግጥ እንደሚገባ በመድረኩ ተሳታፊዎች ተንጸባርቋል፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል እያከናወነ ያለው ህግን የማስከበር ተግባር ፍጥነትና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባም ነው በውይይቱ ወቅት የተነሳው፡፡
እንደሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ሁሉ የትግራይን ህዝብ ነጻነቱን ማቀዳጀት የሚቻለው ህገ-ወጡን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጫንቃው ላይ ማውረድ ሲቻል መሆኑንም የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የትግራይ ተወላጆችን በማቀፍ እኩልነትና ፍትህ የሰፈነባት እውነተኛ ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ መድረኩ ተሳታፊዎች ገለጻ በህወሓት የጥፋት ቡድን በአገር ደረጃ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥሰቶች ዛሬም በትግራይ ክልል እየተፈጸሙ ይገኛሉ።
በመሆኑም በህገ-ወጥ ተግባሩ የቀጠለውን ይህን የጥፋት ቡድን በመደምሰስ ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የልማት ጉዞ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ተወያዮቹ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን አምባዬ እንዳሉት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነቀርሳ የሆነው የህወሓት ቡድን
በየጊዜው በፈጸማቸው የጥፋት ተግባሮች በርካታ ንጹሀን ዜጎች ለሞትና ለጉዳት ተዳርገዋል።
"በመሆኑም እኩይ ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ይህን የጥፋት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ የትግራይን ህዝብ ነጻነቱን ማቀዳጀት ያስፈልጋል፡፡" ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ደረጀ በበኩላቸው ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ ይቅር እንደማይለውና የከፋ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት አገር እንጂ ስልጣን እንደማይጠብቅ ያነሱት ኃላፊዋ፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከትግራይ ህዝብ ጎን በመቆም አጋርነቱን ባረጋገጠው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ድርጊት የሚወገዝ መሆኑን ገልጸዋል።
"ጦርነት የሚከናወነው በፍልሚያው ቦታ በመሆኑ ሁሉም የመንግስት ሠራተኛ እራሱን ከሌብነትና ከአላስፈላጊ ድርጊቶች በማራቅ የተሳለጠ ህዝባዊ አገልግሎት መስጠት አለበት" ያሉት ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሰው ሀብት ልማትና ፐብሊክ ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጥበቡ ናቸው፡፡
አስተያየት የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም የህገ ወጡን ቡድን እኩይ ሴራ ማክሸፍና ያሰማራውን የጥፋት ኃይል በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚቻለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ እራሱንና አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ሲችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጋ በሥራው የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገውን ጦርነት በድል መወጣት እንዳለበትም ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
መንግስት ጥበብና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እያከናወነ ያለውን ህግና ስርዓት የማስከበር ተግባር የጥፋት ቡድኑ በቁጥጥር ሥር እስኪውል ድረስ ማስቀጠል እንዳለበትም ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡