በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ከጀርባ ሆኖ ጥቃት ማድረስ የሀገር ክህደት ነው... የስፖርት ቤተሰቦች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ከጀርባ ሆኖ ጥቃት ማድረስ የሀገር ክህደት ነው... የስፖርት ቤተሰቦች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2013(ኢዜአ) ህዝብና አገርን ከጠላት እየጠበቀ ያለ የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርና ምስጋና ሊቸረው ሲገባ ከጀርባ ሆኖ ጥቃት ማድረስ የአገርና የህዝብ ክህደት መሆኑን የስፖርት ቤተሰቦች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ቤተሰቦች ''ደሜን ለወገኔ'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ ደም ልገሱ።
በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ የሁሉም ስፖርት ፌደሬሽን ሠራተኞችና የስፖርት አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ ማህበር አባላት፣ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች፣ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ማህበር አባለት፣ የማርሻል አርት እና ሌሎች የስፖርት ቤተሰቦች በአራት ኪሎ ስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ተገኝተዋል።
ዛሬ ደማቸውን ከለገሱት የስፖርት ቤተሰቦች መካከል ኢንስትራክተር ኤሊያስ ሙሉ "ህዝብና አገርን ከጠላት እየጠበቀ ያለ የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርና ምስጋና ሊቸረው ሲገባ ከጀርባ ሆኖ ጥቃት ማድረስ የአገርና የህዝብ ክህደት ነው" ብሏል።
መንግስት አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ድርጊቱን የፈጸሙ የህወሓት የጥፋት ቡድን አባላት ከአንድ ኢትዮጵያ ዜጋ የማይጠበቅ አስነዋሪ ተግባር ስለመፈጸማቸው ማሳየት እንዳለበትም ነው የገለጹት።
"ለአገሩ መስዋዕት እየሆነ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደም መስጠት በጣም ትንሽ ነገር ነው፤ ከእዚህም በላይ ድጋፍ በማድረግ አጋርነትን ማረጋገጥ ይገባል" ብለዋል ።
በደም ልገሳ መርሃግብሩ ላይ የተሳተፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ወጣት ዮሴፍ ኃይሌ በበኩሉ የአገር ተምሳሌት በሆነውና የህዝብን ደህንነት ሌት ተቀን እየጠበቀ ባለው ሠራዊት ላይ የጀርባ ጥቃት ማድረስ የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ተናግሯል።
በጥፋት ተግባሩ በተሰማራው የህወሓት አንጃ የተፈጸመው ድርጊት የአንድ ብሔር ወይም ሃይማኖት ጥቃት ሳይሆን የአገር ጥቃት በመሆኑ በአጥፊው ቡድን ላይ እየተወሰደ ላለው እርምጃ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም አረጋግጧል።
ለህዝብና ለሠራዊቱ ያለውን ወገንተኝነት ለማሳያት በዛሬው ዕለት ''ደሜን ለወገኔ'' በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የደም ልገሳ መርሃግብር ላይ በተነሳሽነት መሳተፉንም ነው የገለጸው።
በደም ልገሳው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደም መለገስ ብቻ ሳይሆን የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የስፖርት ቤተሰቦች ደም በመለገስ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ክብር ፈጥነው በማሳየታቸው ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የተጀመረው የደም ልገሳ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ደም የመለገስ ተግባሩ ዛሬ ቀኑን ሙሉ የሚካሄድ ሲሆን በግማሽ ቀንም ከስፖርት ቤተሰቦች 87 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መቻሉን ከመርሃግብሩ አስታባባሪዎች ለማውቅ ተችሏል።