የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ኒጀር አቀና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ኒጀር አቀና
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኒጀር አቻው ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዛሬ ወደ ኒጀር አመራ።
በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዳግም በቀጣዩ ወር ይጀመራል።
በምድብ 11 የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዓርብ ህዳር 4 ቀን 2013 በጄኔራል ሴይኒ ኩቼ ስታዲየም ከኒጀር አቻው ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾች በድምሩ 36 የልዑካን ቡድን አባላት ይዞ ዛሬ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ወደ ኒያሚ ማቅናቱን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ማምሻውን በካፍ አካዳሚ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና በፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን አሸኛኘት ተደርጎለታል።
ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ዛሬ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዋልያዎቹ ከኒጀር ብሔራዊ ቡድን ጋር ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ጀምሮ ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከዛምቢያ ጋር ባደረጓቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች የተሸነፉ ዋልያዎቹ፣ ከሱዳን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሁለት ዓመት ውል ተፈራርመዋል።በውላቸው መሰረትም ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ዋልያዎቹ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች በማዳጋስካር ተሸንፈው፣ ኮትዲ ቯርን አሸንፈው በሶስት ነጥብ ማዳጋስካርን ተከትለው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በአንጻሩ በ63 ዓመቱ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ጂን-ሚሼል ካቫሊ የሚመራው የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በማዳጋስካርና በኮትዲቯር ተሸንፎ በምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።
አሰልጣኝ ካቫሊ የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝነት ከሌላው ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ጂን-ጋይ ዋሌሜን ከተረከቡ ገና አንድ ወራቸው ነው።
ኒጀር ከዋልያዎቹ ጋር ላለባት የጨዋታ ከቻድ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርገው አንድ አሸንፈው፣ አንድ አቻ ወጥተዋል።
በተጨማሪም የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨዋታ አሸንፈዋል።
ላ ሜና (የዱር እንስሳ) በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የኒጀር ብሔራዊ ቡድን በሁለት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች መሸነፋቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ጉዟቸውን በጣም ፈታኝ ያደርገዋል።
አሰልጣኝ ካቫሊ በሁለት ጨዋታዎች መሸነፋቸው የጎዳቸው ቢሆንም፤ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋችን የተንጠለጠለው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሚደረጉት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ ነው ብለዋል።
ለአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ተፎካካሪ የሚሆን ቡድን እየገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና የኒጀር ብሔራዊ ቡድኖች ከዚህ በፊት ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ፣ ኒጀር አንድ ጊዜ አሸንፋለች።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2012 በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን፣ ዋልያዎቹ አንድ ለባዶ ማሸነፏ ይታወሳል።
በፊፋ ወርሃዊ የአገሮች ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 146ኛ ደረጃ ሲቀመጥ፣የኒጀር ብሔራዊ ቡድን 112ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን ሕዳር 8 ቀን 2013 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ያደርጋሉ።