የህወሓት ጁንታ የሀገር መከላከያ ጦር ጄት መትቼ ጥያለሁ የሚለው ፍጹም ሀሰት ነው....ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ጁንታ የሀገር መከላከያ ጦር ጄት መትቼ ጥያለሁ የሚለው ፍጹም ሀሰት ነው....ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ) ጽንፈኛው የህወሓት ጁንታ የሀገር መከላከያ ጦር ጄት መትቼ ጥያለሁ ሲል የገለጸው ፍጹም ሀሰት መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ ተናገሩ።
ሜጄር ጀነራል መሐመድ ተሰማ በሰጡት መግለጫ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በቅርቡ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ጄት መትቸ ጥያለሁኝ ሲል መደመጡን አስታውሰዋል።
"ቡድኑ የአየር ሃይል ጄት የመታሁት በራሴ አየር ሃይል አማካኝነት ነው" ሲል መናገሩንም ነው ሜጄር ጀነራል መሐመድ ተሰማ የገለጹት።
ሆኖም ጽንፈኛው ቡድን ምንም አይነት የአየር ሃይል እንደሌለው ገልጸው፤ ቡድኑ "ጄት መትቼ ጥያለሁ እያለ የሚያሰራጨው ወሬ ፍጽም ሀሰትና የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳ ነው" ብለዋል።
ጽንፈኛው ቡድን በትግራይ ክልል የሚያልፍ ማነኛውም አይነት በረራ ላይ እርምጃ እውስዳለሁ ካለ መግስት ጀምሮ የኢፌዴሪ አየር ሃይል የተመረጡ ቦታዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ ሀፍረቱንና ሽንፈቱን ለመሸፈን የተለያዩ የሀሰት መረጃዎችን እያሰራጨ ይገኛል ብለዋል።
አብዛኛዎቹ የሀሰት መረጃዎችም በፎቶ ሾፕና ከተለያዩ አገሮች በተወሰዱ ምስሎች የተቀነባበሩ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ቦታዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውንም ነው ሜጄር ጀነራል መሐመድ የተናገሩት።
ጽንፈኛ ቡድኑ ይህን ሀቅ በመካድ ህዝብን እያደናገረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
"ነገር ግን ጽንፈኛ ቡድኑ ቦታዎቹ በቁጥጥር ስር አልዋሉም ከማለት በዘለለ ስፍራው ድረስ በመሄድ በተጨባጭ መረጃ ማቅረብ አልቻለም" ብለዋል።
ይህም እውነታው የቱ ጋ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል ነው ብለዋል።
በመሆኑም በጽንፈኛ ቡድኑ በሚፈበረኩ የሀሰት መረጃዎች ህዝቡ ሳይታለል ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሜጄር ጀነራል መሐመድ ጥሪ አቅርበዋል።