ቀጥታ፡

በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሚያኮራ አይደለም---ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2010 በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሚያኮራ አይደለም ሲል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ። በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ ከሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው 17ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው ልዑክ የአቀባበልና ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ አትሌት ኀይሌ ገብረስላሴ በዚሁ የአትሌቶችና ሌሎች የቡድኑ አባላት አቀባበል ላይ ባደረገው ንግግር "ውጤቱ ከጠበቅነው አንጻር የሚያኮራ አይደለም" ብሏል። ነገር ግን በቀጣይ ለሚኖሩ ውድድሮች ብዙ ነገሮችን የሚያስተምር ነው ብሏል ሻለቃ ኃይሌ። "በዚህ ውድድር ማግኘት የሚገባን አራት የወርቅ ሜዳሊያ አጥተናል፤ ይህ ለምን እንደሆነና የተጠበቀው ያህል ውጤት ለምን እንዳልመጣ  ከአሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ጋር በነገው እለት ግምገማ እናካሄዳለን" ብሏል። በዚህ ውድድር የተካፈለው ልዑክ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ሲገባ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ እስከ 400 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማትም ከፌዴሬሽኑ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ የወጣቶች ውድድር ተካፍለው ወርቅ ያመጡ አትሌቶች 25 ሺህ ብርና የብር ሜዳሊያ ያስገኙ ደግሞ 18 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። የነሐስ ሜዳሊያ ያመጡ ደግሞ 10 ሺህ ብርና በተሳትፎ ብቻ ለተመለሱ አትሌቶች ደግሞ የ 3 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ለአሰልጣኞችም እንደየውጤታቸው እስከ 18 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል። ኢትዮጵያ በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ በተካሄደው 17ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሶስት ወርቅ፣ ሁለት ብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያ  ከዓለም አራተኛ ደረጃን ይዛ ነው ያጠናቀቀችው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም