የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ጓዶቻቸው ትርጉም ከሌለው ጦርነት እራሳቸውን እንዲያወጡ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ጓዶቻቸው ትርጉም ከሌለው ጦርነት እራሳቸውን እንዲያወጡ ጥሪ አቀረቡ
መተማ፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) ቆስለው በአማራ ክልል አብርሃጅራ ሆስፒታል እየታከሙ የሚገኙ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ጓዶቻቸው ትርጉም ከሌለው ጦርነት እራሳቸውን እንዲያርቁ ጥሪ አቀረቡ።
ቁስለኞቹ በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና በመከላከያ ሰራዊት ሲያዙ “ግፍና በደል ይደርስብናል” የሚል ስጋት የነበራቸው ቢሆንም እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በተቃራኒው እንደሆነ ተናግረዋል።
እየታከሙ ከሚገኙት የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት መካከል ወጣት ካልዓዩ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በህወሃት ህገ-ወጥ ቡድን ጸያፍ ድርጊት የተቀሰቀሰው ጦርነት ያልተፈለገ ዋጋ አስከፍሎታል።
"ምንም እንኳን በማላውቀው ጦርነት ተሳትፌ ብቆስልም በኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ ድጋፍና ህክምና ተደርጎልኝ እያገገምኩ እገኛለሁ” ያለው ወጣቱ፤ በበረሃ የሚገኙ ጓዶቹ ከማይመለከታቸውና ትርጉም አልባ ከሆነው ጦርነት ራሳቸውን እንዲያወጡ መክሯል።
"የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይል አባላት ከዚህ ህገ-ወጥ ቡድን ራሳቸውን በማግለል ታሪክ ሊሰሩ ይገባል" ብሏል።
ሌላኛዋ የትግራይ ልዩ ኃይል አባል ሰላማዊት ጣዕመ በበኩሏ የትግራይ ህዝብና የፀጥታ ሃይሉ ለህወሃት መጠቀሚያ መሳሪያ ከመሆን ሊታቀቡ እንደሚገባ አስገንዝባለች።
በጦርነቱ ህይወቷን ልታጣ እንደምትችል ስጋት አድሮባት የነበረችው ወጣት ሰላማዊት፤ በሆስፒታሉ የተደረገላት እንክብካቤ ፈጥና እንድታገግም እንዳስቻላት ጠቅሳለች።
ከህክምናው በተጨማሪ በህዝቡ እየተደረገ ያለው እንክብካቤ ሊለያይ የማይችለውን ህዝብ ለመለያየት ብዙ ቢሰራም እንዳልተሳካ የሚያሳይ መሆኑን ገልጻለች።
ይህንን ህዝብ አንድነትና ፍቅር እንዳይኖረው የሚሰራውን ቡድን ለማስወገድ የትግራይ ህዝብ መተባበር እንዳለበትም ገልጻለች።
የአብርሃጅራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ አድማሱ በበኩላቸው "ሆስፒታሉ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ለሁሉም የፀጥታ ሃይል ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እየሰጠን ነው" ብለዋል።
የትግራይ ልዩ ኃይል ቁስለኞች ነፃነት ተሰምቷቸው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ችግሩን ለመቋቋምም ከባህርዳር እና ከሌሎች ሆስፒታሎች ልምድ ያላቸውና የቀዶ ጥገና ሃኪሞች ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት እያገዙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።