የትግራይ ሕዝብ በስሙ ሲነግድና ወንጀሎችን ሲፈጽም የነበረውን ቡድን ከጉያው ማውጣት አለበት...የብልጽግና ፓርቲ አመራር - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ሕዝብ በስሙ ሲነግድና ወንጀሎችን ሲፈጽም የነበረውን ቡድን ከጉያው ማውጣት አለበት...የብልጽግና ፓርቲ አመራር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2013(ኢዜአ) የትግራይ ሕዝብ በስሙ ሲነግድና ወንጀሎችን ሲፈጽም የነበረውን ቡድን ከጉያው በማውጣት ለሕግ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አሳሰቡ።
መንግሥት በሕገ ወጡ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የትግራይ ክልል ሕዝብ እንዲደግፈው ጠይቀዋል።
የፓርቲው ዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር ዛሬ በተደረገ ውይይት ላይ እንዳስገነዘቡት ሕዝቡ በስሙ ሲነግድ የኖረውን ቡድን ለሕግ አሳልፎ መስጠት ይጠበቅበታል።
የትግራይ ሕዝብ አብሮነትን፣ ነጻነትንና አንድነትን የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም ህወሓት የተባለው ከፋፋይ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በስሙ ሲነግድና ወንጀሎችን ሲፈጽም ነበር ብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ ስለ ነጻነቱ የሚያውቅና ለዚህም ሲታገል የኖረ ሕዝብ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ቢቂላ፣ የጥፋት ቡድኑ የኢትዮጵያ የትግል አርማ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ አንገት ለማስደፋት ጥረት ሲያደርግ መኖሩን ገልጸዋል።
ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለመለያየትና ለመነጣጠል ሲያሴር እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ቡድኑ መቀሌ ከመሸገም በኋላ አገሪቱ የግጭትና የትርምስ ቀጠና እንድትሆን ሲሰራ እንደነበርም ተናግረው፤ በሕዝቡም ላይ ኢ-ትፍትሃዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ግፍና በደል ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሕዝቡን ባህልና እሴት የማያውቀው ጽንፈኛ ቡድን ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ለማደብዘዝ ሲሰራ ነበርም ብለዋል።
የትግራይ ተወላጆችና ሕዝብም ነጻነቱን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሕግ ማስከበር ሂደት ለማሳካት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በሕዝብ ስም ሲነግድና ወንጀሎችን ሲፈጽም ለነበረ ሕገ ወጥ ቡድንም መሸሸጊያ መሆን የለበትም ነው ያሉት።
አስተያየታቸውን የሰጡ የትግራይ ክልል ተወላጆች በበኩላቸው ህወሓት ሕዝቡን የማይወክል የጥፋት ቡድን መሆኑን መረዳታቸውን በውይይቱ ወቅት ገልጸው፤ ከመንግሥት ጎን ሆነን ድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።