ህዝቡ ልማቱን እያከናወነ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ አለበት … አቶ ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ልማቱን እያከናወነ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ አለበት … አቶ ተመስገን ጥሩነህ
ባህር ዳር፤ ጥቅምት 29/2013(ኢዜአ) የአማራ ክልል ህዝብ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የቀድሞው የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዛሬው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት "ትህነግ ባለፉት ዓመታት አሳፋሪ ድርጊቶችን ሲፈፅም ቆይቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ የባሰውን አስነዋሪ ድርጊት እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
ትህነግ የኢትዮጵያ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቁ፣ መከፋፈልና ዘረኝነት እንዲነግስ አልሞ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት አቶ ተመስገን፤ በዚህም የተነሳ በሃገሪቱ ታርክ ታይቶ በማይታወቅ አግባብ በአሁኑ ወቅት ብዙ የተወሳሰቡና የተመሰቃቀሉ ችግሮች እንዲፈጠር መደረጉን ገልፀዋል።
ችግሩ በረጅም ጊዜ የተፈጠረና ታስቦበት ሲሰራ የቆየ በመሆኑ በአንድ ጀምበር መፍታት እንደማይቻልም ተናግረዋል።
በተሰራው የሴራ ፖለቲካም ትህነግ በገንዘብም ሆነ በመሳሪያ በመደገፍ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲደርስባቸው እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
“ችግሩን ለመፍታት ዋናውን የችግሩን ምንጭ ማጥፋት ወሳኝ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማድረቅ በተቀናጀ አግባብ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል”ብለዋል።
“ቀደም ሲል በትህነግ ጽንፈኛ ቡድን ሲበደል የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ላይ እራሱ በከፈተው ጦርነት በጋራ በመቆሙ ድል እየተነሳ ነው” ብለዋል።
የትግራይ ህዝብም ከትህነግ ጥቂት ጥቅመኛ ቡድኖች ጭቆና ሳይላቀቅ በጦርነት ልጆቹን እንዲያጣ እየተደረገ በመሆኑ ይህን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በሚደረገው ትግል የበኩሉን እንዲወጣም አቶ ተመስገን ጠይቀዋል።
የትህነግ ጨካኝ ቡድን ማኛውንም አመራጭ ካገኘ አጥፊ ስራዎችን ሊሰራ ስለሚችል የክልሉ ህዝብ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
“በገጠርም ሆነ በከተማ ፀጉረ ልውጥ ሰው ሲመለከት እንዲሁም ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎችን ሲያይ በአፋጣኝ በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ሃይል በመጠቆም ጥፋት እንዳይደርስ ማድረግ ይገባል”ብለዋል።
''ጦርነት አውዳሚና ኢኮኖሚን የሚጎዳ ነው''ያሉት አቶ ተመስገን “አካባቢን ከመጠበቅ በዘለለ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ሌሎች የልማት ስራዎችን እንደከዚህ ቀደሙ ጠንክሮ መስራት ይገባል”ብለዋል።
የተጀመረው ጦርነት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅም በግንባር ላለው የፀጥታ ሃይልና በጦርነቱ ለሚፈናቀሉ ዜጎች በተደራጀ አግባብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
“በአጥፊው የትህነግ ቡድን ላይ በብልሃት፣ በጥበብና በትዕግስት የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት መከናወን አለበት” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው።
“በኮሮና ቫይረስና በአንበጣ መከሰት ጫና የደረሰበት የክልሉ ኢኮኖሚ አሁን በተጀመረው ጦርነት ክፉኛ እንዳይጎዳ ልማቶችን በትኩረት ማከናወን ይገባል”ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ የትህነግ ዘመኑን ያልዋጀ አስተዳደርና በደል በቃኝ በማለት የተጀመረው ትግል በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉበኤ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ ምትክ አቶ አገኘሁ ተሻገርን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ በመሾም ተጠናቋል።