ቀጥታ፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሁመራ ሱዳን መንገድን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጠረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2013(ኢዜአ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማይዳሊ፣ ዳንሻ፣ ባዕከር፣ ልጉዲ፣ የሁመራ አየር ማረፊያ እንዲሁም የሁመራ ሱዳን መንገድን መቆጣጠሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ተናገሩ።

ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ስልጣንን በሃይል ለመቆጣጠር  በማለም የህዝብ አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት  ማድረሱን አስታውሰዋል።

ጥቃቱንም እንደ መብራት ሃይልና ቴሌኮሚኒኬኝን  ያሉ መሰረተ ልማቶችን በማጥፋትና በተቀነባበረ መንገድ መከናወኑን ነው የገለጹት።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥቃቱን በአኩሪ ገድል ተከላክሎ በወሰደው እርምጃም በርካታ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሰራዊቱ በምዕራብ ግንባር በኩል ባደረገው የማጥቃት እርምጃ የሁመራ አየር ማረፊያን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስረድተዋል።

በተለይ ጽንፈኛ ቡድኑ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከወን የተዘጋጀበት የሁመራ ሱዳን መንገድም በሀገር መከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢ ያሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍና አለኝታነት በተግባር እያሳዩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን የማጥቃት እርምጃ አጠናክሮ  እንደሚቀጥልም  ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ገልጸዋል።

ተገደው ለጽንፈኛው ቡድን ህወሃት እየተዋጉ የነበሩ በርካታ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ለአገር መከላከያ ሰራዊት እጃቸውን እየሰጡ እንደሆነም ገልጸዋል።

አብዛኛው የልዩ ሃይል አባላት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑና ለወታደርነት ያልደረሱ መሆናቸውን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ፤ “ይህም ወደጦርነት የሚልካቸው ቡድን ለስልጣን እንጂ ለዜጎች ግድ የሌለው መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

ለምን እንዋጋለን የሚል ጥያቄ የሚያነሱትን የልዩ ሀይል አባላትን ደግሞ  ጽንፈኛው ሃይል የጥይት እራት እያደረጋቸው ይገኛል ብለዋል።

ጽንፈኛው ቡድን አሁን ላይ ያሉትን መሳሪያዎች በማስረከብ የሽንፈትን ካባ እየተከናነበ መሆኑንም አስረድተው፤ ይህ ቡድን ያሰበው እንደፈለገው አልሆንለት በማለቱ የተለያዩ  የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን እያሰማ ይገኛል ብለዋል።

ጽንፈኛው ቡድን በአንድ በኩል ወጊያውን መንግስት እንደጀመረውና እርሱ እያሸነፈ እንደሆነ፤  በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብ ውጊያውን እንዲያስቆም ጥሪ በማቅረብ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሃሳቦችን እያራመደ መሆኑንም ነው ያነሱት።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ እያሳየ ያለው ድጋፍ ከፍ ያለ የሞራል ልእልና እንዳላበሰው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ መግለፃቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም