ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የመሬት ወረራ ችግርን የሚያጠና ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ጠቆሙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የመሬት ወረራ ችግርን የሚያጠና ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ጠቆሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ወረራና የግንባታ ችግርን አጥንቶ መፍትሄ የሚያመላክት ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጠቆሙ።
በመዲናዋ የሚስተዋለውን የመሬት ወረራ ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
ምክትል ከንቲባዋ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ የመሬት ወረራ ችግር ስፋት ያለው የጋራ ችግር ሆኖ ዘልቋል።
በመሆኑም አስተዳደሩ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
“ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት የሚቻለው የጋራ አገራዊ ሃብቶችን መጠበቅ ሲቻል ነው” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ችግሩን ለመፍታት በጋራ ኃላፊነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
“እየተስፋፋ የመጣውን የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታ ችግር ለማጥናትና መፍትሄ ለማመላከት ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ይቋቋማል” ብለዋል።
ከከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት፣ በየደረጃው ካሉ አመራሮች፣ ከፍትህ ተቋማት፣ ከመሬት ልማት፣ ከፖሊስና ከሌሎችም አካላት የተውጣጣ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።
በየደረጃው ያለ አመራር ሁሉም ኃላፊነት ወስዶ ከሰራ ችግሩን ማስተካከል እንደሚቻልም አመልክተዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ችግሩ ወደየትም የሚገፋ ሳይሆን በጋራ መፍትሄ የሚፈለግለት ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ የደንብ ማስከበር ዘርፍ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ ችግሩን በሚመለከት የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሁፋቸውም ለመዲናዋ የመሬት ወረራ የተስፋፋው ተቋማት በተናጠልም ይሁን በጋራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ባለመቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሥነ ምግባር ችግርና ሌብነትም ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሬት ወረራ ላይ በስፋት የሚሳተፉት ባለሃብቶችና ህገ ወጥ ደላሎች መሆናቸውንም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።
“በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደንብ ማስከበር፣ የአስተዳደር አካላት፣ ፖሊስ፣ የፍትህ አካላትና ዐቃቤ ህግ ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር አለባቸው” ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የችግሩን ስፋትና ወንጀሉን ለመከላከል ማነቆ ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች አንስተዋል።
በተለይም የህግና የአሰራር ክፍተቶች፣ የህገ ወጥ ደላሎች መበራከትና በመሬት ወረራ ላይ በብዛት ተሳትፈው የሚገኙት ባለሃብቶች ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል።
የአስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ የመሬት ሃብትን መጠበቅ በየደረጃው ያለ አመራር ዋነኛ ሥራ ሊሆን ይገባል።
የፍትህና የፀጥታ አካላትም የመሬት ወረራን ለማስቆም ህግ የማስከበር ሃፊነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
222 SharesLikeCommentShare