ቀጥታ፡

የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ኢትዮጵያን ከጠላት ለመከላከል መስዋዕትነት ለመክፈል ያላቸውን ዝግጁነት ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2013 ( ኢዜአ) የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ኢትዮጵያን ከጠላት ለመከላከል መስዋዕትነት ለመክፈል ያላቸውን ዝግጁነት ገለጹ።

አባላቱ ጸረ-ህዝቡ የህውሃት ቡድን ለጥፋት ሊያውላቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ባይደመሰሱ ኖሮ፤ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችል ነበር ብለዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው የቀድሞ የሰራዊቱ አባላት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገርን ክብርና አንድነት ለመጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልና መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ያገለገሉት ኮሎኔል ተፈራ እሸቴ የኢትዮጰያ ሰራዊት ከአገር አልፎ በአፍሪካ አህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ስምና ዝና እንዳለው ጠቅሰዋል።

እንደ ኮሎኔል ተፈራ ገለጻ፣ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ለስልጣን ጥማቱ ሲል ሲጠብቀው የነበረው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ ከአገር ክህደት በላይ ነው።

“ድርጊቱ በኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ከመሆኑ ባለፈ ከሰራዊቱ ባለፈ፤ ሲቪል ዜጎችንም በእጅጉ ያስቆጣ ነው” ብለዋል።

በአገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ትምህርት ቤት በአሰልጣኝነትና በአስተዳደር ፋይናንስ ኃላፊነት እስከ 2002 ዓ.ም ያገለገሉት ሻለቃ ወንዱ ወልዴ በበኩላቸው “ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት ጸረ-ህዝብና ጸረ- አገር መሆኑን ያሳየ ነው” ብለዋል።

ጸረ-ሰላምና ልማት ቡድኑ የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት ከፍራቻና ከአላዋቂነት በመቁጠር የኢትዮጵያ መከታ በሆነው ሰራዊትላይ ጥቃት መፈጸሙን አንስተው፤ ድርጊቱ ቡድኑ ድርድር የማያስፈልገውና በይቅርታ መታለፍ እንደሌለበት ያሳያል ብለዋል።

የቀድሞ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ኃይሎችን ለመመከት ወደ ኋላ እንደማይሉ አባላቱ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ እነሱም ሆኑ ሌሎች ጓዶቻቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ከህወሓት ውጪ ያሉና የኢትዮጵያን ልማት የማይፈልጉ የውስጥም የውጭም ኃይሎች እኩይ ተግባራቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝቡ አንድነቱን ማጠናከርና አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም