ቀጥታ፡

የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰራዊቱ ላይ የፈፀመውን ክህደት እናወግዛለን-ፖለቲካ ፓርቲዎች

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን የክህደትና የሽብር ወንጀል በጽኑ እንደሚያወግዙ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

በክልሉ የሚገኙ የብልጽግና፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ነጻነት ንቅናቄና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የፓለቲካ ዛሬ በጋራ መግለጫ አውጥተዋል ።

ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባወጡት ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የክህደትና የሽብር ወንጀል በጽኑ አውግዘዋል።

ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የጥፋት ኃይሎችን በማሰማራት በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም አውግዘዋል።

የህወሓት ጁንታ የጥፋት ኃይል እያካሄደ ያለውን ሀገር የማፍረስ ዓላማ ለማስቆምና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል ።


ከሰራዊቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።


የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ አዲስ ጊዜያዊ አሰተዳደር እንዲቋቋም ያሳለፈውን ውሳኔ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል ።

የጥፋት ኃይሉ ተስፋ ስለቆረጠ በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኖችን በማሰማራት ተጨማሪ ጥፋት እንዳያደርስ ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


የትግራይ ህዝብን ከጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ጋር በፍጹም አንድ አድርገው እንደማይመለከቱት በመግለፅ ህዝቡ የጽንፈኛውን እኩይ ዓላማ በመገንዘብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።


የጥፋት ቡድኑ ለጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች ተገደው ወደ ጦርነት እንደገቡ በመጠቆም፤ ለሀገራቸውና ለቤተሶቦቻቹው ሲሉ እጃቸውን በሰላም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሰጡ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም