ህወሀት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት የሚወገዝ ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ህወሀት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት የሚወገዝ ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች
ጋምቤላ፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው የክህደት ድርጊት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
መንግስት በጥፋት ቡድኑ ላይ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፓርቲዎቹ አሳስበዋል።
ብልጽግናን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ሰሞኑን የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ተግባር አሳፋሪ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ተወካይ አቶ ተዘራ ኃይለማሪያም እንዳሉት የህወሓት የጥፋት ቡድን የሀገርን ዳር ድንበር እየጠበቀ ባለው ሰራዊት ላይ የፈጸመው የክህደት ተግባር አሳፋሪና የሚወገዝ ነው።
“ሀገርን ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ህዝባዊነቱን እየተወጣ ላለው ሰራዊት ፍቅርና ድጋፍ መስጠት ሲገባ ባልጠበቀው መልኩ ተኩስ በመክፈት ጉዳት ማድረስ ከሀዲነት ነው” ብለዋል።
በሰራዊቱ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ፓርቲያቸው አጥብቆ እንደሚያወግዘው በመግለጽ መንግስት ለጀመረው እርምጃ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ፓርቲው ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
“የስልጣን ጥመኞች በህዝቦች መካከል የጥላቻ መርዛቸውን በመርጨትና ግጭት በመፍጠር የዜጎች ህይወት እንዲጠፋና ህዝቡ እንዲለያይ እየሰሩ ነው” ብለዋል ።
ህዝቡ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
“የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ላይ የፈጸመው ድርጊት ሀገርን ለማፈራረስና የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ የሰነቀን ዓላማ ማሳያ ነው” ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቲቾት ኮመዳን ናቸው ።
የጥፋት ኃይሉን እኩይ ተግባር ለማክሸፍ የተጀመረው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር በመሆን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ የጽህፈት ቤት ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ኡማን አግዋ በበኩላቸው “ህወሓት ህብረ-ብሔራዊነትንና ህዝባዊነትን በተላበሰው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ድርጊት በሀገር ላይ የተቃጣ ትንኮሳ ነው” ብለዋል።
ዳር ድንበር ከመጠበቅ ጎን ለጎን አርሶ አደሩን በግብርና ልማት በማገዝ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ በሚገኘው ሰራዊት ላይ የህወሓት የጥፋት ቡድን የማይገባ ድርጊት መፈጸሙን ተናግረዋል ።
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጥፋት ቡድኑ ላይ የጀመረውን እርምጃ ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ አስታውቀዋል ።