ባድሜንተንን ከቤት ውጭም ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው -ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ባድሜንተንን ከቤት ውጭም ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው -ፌዴሬሽኑ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን ውድድሮችን ከቤት ውጭም ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ።
ከዚህ በፊት ውድድሮች በቤት ውስጥ ብቻ ተወስነው ቆይተዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ የእስያ አገሮች ስፖርቱን ከቤት ውጭ ለማካሄድ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን የዓለም አቀፍ ባድሜንተን ፌደሬሽን ውድድሮችን ከቤት ውጭ የሚካሄድባቸውን መንገዶች ለአባል አገሮች እያስተዋወቀ ነው።
የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ባለሙያ አቶ ዬሴፍ ለታ ለኢዜአ አንዳስረዱት በኢትዮጵያ የባድሜንተን ስፖርትን ከቤት ውጭ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ከቤት ውጭ የሚካሄደው ውድድር በቤት ውስጥ ከሚካሄደው ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ በቤት ውስጥ በአንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ ይደረግ የነበረው ውደድር ከቤት ውጭ ሲካሄድ እስከ ሶስት ሰዎች ያሳትፋል ።
እንዲሁም የመጫወቻ ሻተሯን ጨምሮ የተወሰነ ልዩነት እንዳለው ባለሙያው ተናግረዋል።
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት እታለማሁ ተሰማ ባድሜንተንን በቀላል ወጪና በአነስተኛ ቦታ ማዘውተር ይቻላል ይላሉ።
ሆኖም በአገሪቱ ስፖርቱን ባለመተዋወቁ ''በሚፈለገው ልክ'' እንዳልተስፋፋ ይገልጻሉ።
ከኦሎምፒክ ስፖርት አንዱ የሆነው ባድሜንተን በኢትዮጵያ ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እንዳስቆጠረ ይነገራል።
በስፖርቱ ውጤታማ ስፖርተኞችን ማፍራት ከተቻለ ለአገር ገጽታ ግንባታና የገቢ ምንጭ እንደሚሆንም ይታመናል።
ባድሜንተን የሰውነትን ክብደትን ለመቆጣጠር ፣ለጥሩ የደም ዝውውር፣ ራስን ለማዝናናትና ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉት ባለሙያዎች ይናገራሉ።