የህወሀት የጥፋት ቡድን ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-የአርባምንጭ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሀት የጥፋት ቡድን ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-የአርባምንጭ ነዋሪዎች
አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) መንግስት የጽንፈኛውን የህወሀት ቡድን ትንኮሳ ለመግታት የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ነከረ ነጋሽ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ዘራፊው ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ያልተጠበቀ አረመንያዊ ድርጊት ነው።
"የቡድኑ አባላት በስልጣን ዘመናቸው የህዝብና የሀገርን ሀብት መዝረፋቸው ሳያንስ ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያለው ፀያፍ ተግባር የህዝብና የመንግስትን ትዕግስት አስጨርሷል" ብለዋል ።
"የጥፋት ቡድኑ ህዝብና መንግስት ያሳየውን ትዕግስት እንደ ፍርሃት በመቁጠር በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠራል" ሲሉም ተናግረዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር የቡድኑን እኩይ ተልአኮ ለመግታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
"ፅንፈኛው ኃይል በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አሳፋሪ ተግባር የኢትዮጵያን ህዝብ ይበልጥ የሚያስተሳስር ነው" ያለው ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወጣት ፍሬው ደለለኝ ነው።
መንግስት የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ የጀመረውን እርምጃ ከዳር በማድረስ የህዝቡን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
"የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል" ያለው ወጣቱ የጽንፈኛውን የህወሀት ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ለመግታት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ስኬታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ወይዘሮ ሳራ ተፈራ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከትግራይ ክልል በግድ ወደ ጦርነት እንዲዘምቱ የተደረጉ ኃይሎች እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት በመስጠት ሰላም ወዳድነታቸውን በተግባር ሊያረጋግጡ ይገባል" ብለዋል።
መንግስት በጥፋት ቡድኑ ላይ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወይዘሮ ሳራ ጠይቀዋል ።