ቀጥታ፡

የሃገራችንን መዋቅራዊ ችግር ለመፍታት ከሃዲው ቡድን መወገድ ይኖርበታል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም (ኢዜአ) “ረጅም ጊዜ የቆየውን የሃገራችን መዋቅራዊ ችግር በማያዳግም አግባብ ለመፍታት የህወሃት ከሃዲ ቡድን መወገድ ይኖርበታል” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

“ላለፉት ዓመታት በህወሃት ቡድን ቅጥያጣ ጥፋትና ድፍረት "ትዕግስታችን" እንደ ፍርሃት እንዲሁም "አስተዋይነታችን" እንደ ድክመት እየተቆጠረ ህዝብና መንግስት ከልክ ያለፈ ዋጋ እንዲከፍሉ ማስገደዱ ይታወሳል” ብለዋል።

ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ-ጠሉ ከሃዲ ቡድን ከቀናት በፊት የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ኃይል ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰው፤ “በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱ የአማራን ህዝብ ለመውረር በጠገዴ ቅራቅርና ሶሮቃ አካባቢ ያካሄደው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲሁም እስከ ጎንደር ለመዝለቅ ያሳየው ንቀት፣ እብሪት እና ድፍረት እጅግ አሳፋሪ መሆኑ ልብ ይሏል” ብለዋል።

የከሃዲውን ቡድን ረጅም ህልም በአጭሩ የቀጩት የመከላከያ ሃይል፤ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻዎች ፈጣን የአጸፋ ምላሽ በመውሰድ ያስመዘገቡት ውጤት በእጅጉ የሚደነቅና የሚያስመሰግን እንደሆነም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።


“በከሃዲ ቡድኑ ሴራ ለዘመናት ሰምና ወርቅ ሆኖ የኖረው የአማራ እና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት በዋዛ የሚበጠስ ሳይሆን፤ ታሪካዊ አንድነታቸውና የተጋመደው ህብረታቸው እየጠበቀ ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋገር ይሆናል” ብለዋል።


“ረጅም ጊዜ የቆየውን የሃገራችን መዋቅራዊ ችግር በማያዳግም አግባብ ለመፍታት ይህ ከሃዲ ቡድን መወገድ ይኖርበታል” ያሉት አቶ ደመቀ፤ በተለያየ አቅጣጫ ከቡድኑ ጋር አብረው የሚሰሩ ሃይሎች በየአካባቢው ተጨማሪ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ በፍጥነት መነቀል እንዳለባቸው ገልጸዋል።


“የመከላከያ ኃይላችን የጀመረው ዘመቻ ፍጥነትና ጥንቃቄን በሚዛን አስቀምጦ የሚጓዝ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፍጥነትና ጥንቃቄው ከሃዲውን ቡድን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብና ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ከጉዳት ለመጠበቅ በማለም እንደሆነ አብራርተዋል።


“በአሁን ጊዜ የመከላከያ ሃይላችን በተለያዩ ግንባሮች ግዳጁን በብቃት እየተወጣ አኩሪ ገድል ማስመዝገቡን ቀጥሏል” ሲሉ ገልጸዋል።

ለተጀመረው ዘመቻ ውጤታማነት ህዝቡ ከመከላከያ ሃይሉ ጎን በመቆም ታሪካዊ ደጀንነቱን በተግባር በማረጋገጥ ትውልድ እና አገርን በማዳን ተልእኮ ላይ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም