ቀጥታ፡

አገር ለማፍረስ የሚሰሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች ሴራ በጋራ ትግል ይከሽፋል - የአማራ ክልል ምክር ቤት

ባህር ዳር፣ ጥቅምት 29/2013 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ የፖለቲካ ቁማርተኞችን ሴራ ለማክሸፍ የኢትዮጵያ ህዝቦች የበለጠ አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ሊቆሙ ይገባል” ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ተናገሩ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 16ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ሲጀመር አፈ ጉባኤዋ እንደገለጹት፤ የአማራ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን አንድነቷ የጠነከረ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከጥንት እስከ ዛሬ እየሰራ ይገኛል።

“ኢትዮጵያ በህዝቦች መስዋትነትና አብሮነት እንዳትፈርስ ሆና በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባች ጠንካራ አገር ናት” ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ በስልጣን ላይ የቆየው የትህነግ ሃይል በህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስና ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት አገርን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

“ለዚህም አገርና ህዝብን በመጠበቅ ተልኮውን እየተወጣ ባለው መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት በመፈፀም የለየለት ከሃዲ መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል” ብለዋል።

በተላላኪው ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ አሳዛኝ ጭፍጨፋ መደረጉን ገልፀው፤ ጥቃቱ የተፈፀመው በአማራ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ይበልጥ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን አጠናክሮ እንዲተባበር የሚያደርገው መሆኑን ጠቅሰው፤ “በተግባርም እየታየ ያለው ይሄው ነው” ብለዋል።

የአማራ ህዝብ በፀረ ሰላም ሃይሎች ግፍና መከራ እየደረሰበትም ቢሆን በኢትዮጰያዊ አንድነቱ ለአፍታም ቢሆን የማይደራደር ፅኑ ህዝብ መሆኑን አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።

“ህዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ ካለው ኩራት የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተሰባጥሮ ህግና ስርዓት አክብሮ ሃገሩን በማልማት ግንባር ቀደም ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው” ብለዋል።

ነገር ግን የህዝቡን አንገት ለማስደፋትና አገርን ለመበተን ፍላጎት ባላቸው የትህነግና ኦነግ ሸኔ ቡድን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየተፈጸመ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

“በደምና በአጥንት ተጋምዶ፣ ክፉ ደጉን በጋራ ያሳለፈው የትግራይ ህዝብ ከአማራ ወንድም ህዝብ ጋር በማጋጨት ትህነግ ጦርነት ከፍቷል” ብለዋል።

የተከፈተውን ጦርነት በመከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የፀጥታ ሃይል በመመከት የአገር አፍራሽ ቡድኑ ሴራ እንዲከሽፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ወደፊት በሌሎች ህዝቦች ላይ መፈጸሙ አይቀሬ በመሆኑ የትህነግን ቡድን በጋራና በትብብር ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት ሊቀጥል የሚችለው በህዝቦች መካከል መቻቻልና አብሮነትን በማጠናከር በመሆኑ መላው ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ በወቅታዊ ክልላዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥና የተለያዩ ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም