ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተገቢና ምክንያታዊ ናቸው...የፖለቲካ ፓርቲ አ መራሮች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2013(ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተገቢ፣ ምክንያታዊና ሕገ-መንግስቱን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ። 

መንግስት በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጀመረውን ስራ ሳያወላውል መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት በክልሉ እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች ዜጎች እንዳይጎዱ እያደረገ ያለውን ጥንቃቄ አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ ተገቢነት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

እርምጃ የሚወሰድበት "የህወሃት ቡድን" ተስፋ የቆረጠ በመሆኑ ዜጎችን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ሊጠቀም ስለሚችል የኦፕሬሽን ስራው በዘዴ፣ በስልት፣ በእርጋታና መሬት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማጥናት ሊከወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የዚህ ዓይነት ወታደራዊ ተልዕኮዎች ሲኖሩ ዜጎችን መሳሪያ አድርጎ የጥቃት ሰለባ ማድረግ የተለመደ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስትም ሊገነዘበው የሚችለው እንደሆነ ነው ያስረዱት።

በመሆኑም መንግስት የሚወስዳቸው ሁሉም እርምጃዎች "በችኮላ ሳይሆን በጥሞና" ሕዝብ ተጎጂ በማይሆንበት መልኩ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተገቢና ምክንያታዊ እንደሆኑና ሕገ-መንግስቱ በሰጠው ስልጣን መሰረት የተወሰኑ እንደሆኑም ገልፀዋል።

ሕግን በጣሰ መልኩ ምርጫ በማካሄድ ስልጣን ላይ የሚገኘውን የትግራይ ክልል መንግስት አፍርሶ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑም ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።

በሰለጠኑ ባለሙያዎች /ቴክኖክራቶች/ ብቻ ጊዜያዊ መንግስት እንደሚቋቋምና ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ጊዜያዊ መንግስት እንደሚመሰረት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉም ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ ይበጃል ባለው መልኩ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሊቋቋም እንደሚገባና መንግስት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር በየነ ያብራሩት።

የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በሕዝብ ያልተመረጠ በመሆኑ የቆይታ ጊዜው እስከ አገራዊ ጠቅላላ ምርጫው ድረስ መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።

"ከህወሓት ጋር ያለው አለመግባባት በሕጋዊና በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ቢደረግም ጦርነትን አማራጭ አድርገው በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ነው" ብለዋል የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ።

የአገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጸም ያለው የመጨረሻ አማራጭ ሃይል መጠቀም በመሆኑ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል።

አሁን ሽምግልና ተቀባይነት እንደሌለውና መንግስት አጥፊዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም አክለዋል።

መንግስት የሰዎች ግድያና ንብረት ማውደም ላይ የተሳተፉትን የህወሓት አመራሮች በመያዝ ለፍርድ ማቅረብ እንዳለበትም ተናግረዋል።

የተጀመረውን ተልዕኮ ባጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰብል መሰብሰብ እንዲሁም ወደ ዕለት ተዕለት ስራዎቹ እንዲመለስ ማድረግም ይገባል ብለዋል።

መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጀመረውን ስራ ሳያወላውል መቀጠል፤ ሕዝቡም አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት ትብብር ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የአንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉም መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎችና፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔም ተገቢነት ያለው ነው የሚሉትን ሀሳቦች ይጋራሉ።

"የህወሓት ቡድን" ራሱን ለመከላከል ንጹሃን ዜጎችን ሰብዓዊ ጋሻ በማድረግ ሰለባ ከማድረግ ወደኋላ ሰለማይል የሚወሰዱ እርምጃዎች ብስለት የታከለባቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

እርምጃዎች ከመወሰዳቸው በፊት ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ወረቀቶች መበተንን ጨምሮ የተለያዩ የመልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በሕግ እየተፈለጉ ያሉት የህወሓት አመራሮች ሕዝቡ ውስጥ እንደሚደበቁ ግልጽ ነው ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ እነሱን የመያዝ ስራ ፈተናዎች ሊገጥመው ቢችልም የጸጥታ አካሉ በተጠና መንገድ ተፈላጊዎቹን የማደን ስራውን ማከናወን እንደሚገባው ገልጸዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ሕዝቡን ለማረጋጋትና እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ ጉዳዮችን ለማጥራት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ ሠላም ለማስፈንና ልማት ለማረጋጋጥ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው አቶ ትዕግስቱ ያስረዱት።

መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው ኦፕሬሽኑ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ልማትና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች በፍጥነት መመለስ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም