ቀጥታ፡

መንግስት በህወሃት የጥፋት ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንደግፋለን…የሲዳማ ክልል የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ሀዋሳ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) የጥፋት ኃይል የሆነውን የህወሃት ቡድን ከትግራይ ህዝብ በመነጠል ለሕግ ለማቅረብ በሚወሰደው እርምጃ ከመንግስትና ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆም የሲዳማ ክልል የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ ፡፡ 

ምክር ቤቱ ይህንን ያስታወቀው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ ከመከረ በኋላ በሰጠው መግለጫ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የሲዳማ ክልል የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባልና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ /ሲአን/ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተገኝ ወልዴ እንዳሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተገነባ ህብረ-ብሔራዊ ተቋም ነው።

“የሲዳማ ህዝብ ሲታገልለት የቆየውን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነፍጎ የቆየው የህወሃት የማፍያ ቡድን በአሁኑ ጊዜ ሀገርን የማፈራረስና የመበተን ዓላማ አንግቦ ለሀገር አለኝታ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ከሃዲ ቡድን መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል።

“የህወሃት የጥፋት ቡድን የሀገሩን ዳር ድንበር ቀን ከሌሊት በመጠበቅ ላይ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ካምፕ ላይ የፈፀመው ጥቃት ሀገር የማፍረስ ተግባርና በሉአላዊነታችን ላይ የተቃጣ አሳፋሪ ተግባር ነው” ብለዋል።

ይህ ቡድን መሸሸጊያ ካደረገው ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ በመነጠል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕግ ለማቅረብ የሚደረገውን እርምጃ ለመደገፍም የጋራ ምክር ቤቱ ከመንግስትና ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆም ነው የገለፁት።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሽብር ተግባር ሲያከናውን የነበረው ቡድኑ በሲዳማ ክልል ቦታ እንዳይኖረውና በክልሉ አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን ምክር ቤቱ ከህዝቡ ጋር በመተባበር እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የሲዳማ ብልጽግና ፓርቲ፣ሲአን፣የሲዳማ ሃዲቾ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የሲዳማ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም የሲዳማ አንድነት ፓርቲ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም