የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን የገቢ ምንጩን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን የገቢ ምንጩን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት የገቢ ምንጩን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታውቀ።
የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።
በጉባኤው በፌደሬሽኑ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ የ2012 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ጸድቋል።
በመድረኩ የባድሜንተንን ስፖርት ከቤት ውጪ ለማካሄድ የሚያስችል የፕሮግራም ትውውቅም ተደርጓል።
በጉባኤው ላይ የፌደሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት እታለማሁ ተሰማ መንግስት የስፖርት ማህበራት በገቢ እራሳቸው እንዲችሉ የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽንም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተያዘው በጀት ዓመት የገቢ ምንጩን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚያከናውን ተናገራዋል።
"ይህን ዕቅድ እውን ለማድረግ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ጋር ግንኙን በመፍጠር ይሰራልም" ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በ2013 ዓ.ም የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ስልጠናዎች እንደሚዘጋጁ ነው የጠቆሙት።
ከዓለም አቀፉ ባድሜንተን ፌዴሬሽንና ከአፍሪካ ባድሜንተን ኮንፌደሬሽን ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ ስፖርቱን ለማስፋፋት ሰፊ ሥራዎች ለመስራት መታቀዱንም ተናግረዋል።
ፌደሬሽኑ ባለፈው 2012 በጀት ዓመት በኮቪድ -19 ወረርሽኝም ውስጥ ሆኖ የእቅዱን 85 በመቶ መፈጸሙ በመድረኩ ተገልጿል።
የፌደሬሽኑ ጥንካሬ ተብለው ከተነሱት መካከል በተለይ ከዓለም አቀፉ ባድሜንተን ፌዴሬሽንና ከአፍሪካ ባድሜንተን ኮንፌደሬሽን የተለያዩ የስልጠና ቁሶች ድጋፍ እንዲገኝ መደረጉና በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ብሄራዊ ቡድን በማዘጋጀት መሳተፍ መቻሉ የሚጠቀሱ ናቸው።
ይሁን እንጂ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የታዳጊ ወጣቶች ስልጠናና ለሁሉም ከፍት የሆነ ውድድር መከወን አለመቻሉ በክፍተት ተነስቷል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች የባድሜንተን ክለቦች እንዲጠንከሩ የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩና የማዘውተሪያ ቦታና ስፍራ ለማስፋፋት ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ስፖርቱን ማስተዋወቅ የሚያስቸሉ ሥራዎች በሰፊው ሊሰሩ እንደሚገባና የገቢ ምንጭ ለማጠናከር ከተቀመጠው ዕቅድ ባለይ ብዙ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው ፌደሬሽኑን በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሪዚዳንትነት ለስምንት ዓመት ያገለገሉትን አቶ ገብረየሱስ አየለ እንዲሁም አቃቢ ንዋይ በመሆን ለአራት ዓመት ያገለገሉትን አቶ ጸሐዬ ሀጎስን በክብር አባልነት በማካተት ተጠናቋል።