ቀጥታ፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲውን በመጠቀም መንግሥት የሚያከናውነውን ሕግ የማስከበር ተግባር ለተለያዩ አካላት ማስገንዘብ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2013 (ኢዜአ) የፐብሊክ ዲፕሎማሲውን በመጠቀም መንግሥት የሚያከናውነውን ሕግ የማስከበር ተግባርና ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት እያከናወነ ያለው ተግባር በአገሪቱ የሚካሄደው ለውጥ አካል ነው።

በለውጡ ህግን የማስከበር ስራዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ “በትግራይ ክልልም መንግስት በአሁኑ ወቅት ህገወጥ በሆነ ቡድን ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ በዜግነት መርህ ዲፕሎማሲ ሁሉም እንዲያውቀው ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።

ይህ ህግ የማስከበር ስራ ጎረቤት አገሮችን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያውቀው ተግባር ቢሆንም የፐብሊክ ዲፕሎማሲውን በመጠቀም በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ከስር ከስር ማሳወቅ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።

“መንግስት አንድ ዘራፊ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ የእርስ በርስ ግጭት ተደርጎ እንዳይታይ መስራት ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

“ዴሞክራሲ ከህግ የበላይንት ውጪ ሊረጋገጥ የማይችል እውነታ ነው” ያሉት አቶ እንዳለ፤ እርምጃ እየተወሰደበት ያለው ቡድን ዴሞክራሲ እንዲሸረሸርና ሃገራዊ ሃብትን ለቡድን ጥቅም ሲያውል እንደነበር አስታውሰዋል።

“መንግስት ይህንን ለማስተካከል እየሰራ እንደሚገኝ ማሳወቅ ይገባል” ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን፣ ነጋዴዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ዲፕሎማቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ መንግስት ስለሚወስደው ህግን የማስከበር ተግባር ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

የዲፕሎማሲና አለም አቀፍ ግንኙነትና መምህሩ አቶ እንዳለ እንደሚሉት፤ መንግስት የሚወስደውን ህግን የማስከበር ርምጃ በየአገሩ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በዝርዝር ማስረዳት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሰጠውን ማብራሪያ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም