ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 2 አዳዲስ ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖችን ተረከበ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2017 ካዘዛቸው አሥር ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖች መካከል ሁለቱ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

አውሮፕላኖቹ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በስፔን ከሚገኝ አቪዬሽን ሳንሲፎንትሬስ በጎ-አድራጎት ድርጅትና ከኤር ባስ ፋውንዴሽን የተበረከቱ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ፣ አልጋና ዊልቼሮችን አጓጉዘዋል።

ቦሌ አየር መንገድ ሲደርሱም የአየር መንገዱ ዋና ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር አቶ መስፍን ጣስው፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂና የአየር መንገዱ ሠራተኞች አቀባበል አድርገዋል።

አየር መንገዱ እ.አ.አ በ2017 ካዘዛቸው አሥር ኤር ባስ ኤ-350 መካከል ቀሪዎቹ ስምንት አውሮፕላኖች በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚገቡም አቶ መስፍን ገልፀዋል።

የአዳዲሶቹ አውሮፕላኖች መምጣት ለአየር መንገዱ ፈጣን የዕድገት ዕቅድ ስኬት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

አዳዲሶቹ አውሮፕላኖች ያጓጓዙት የሕክምና ቁሳቁስ አየር መንገዱ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ሲያስገባ የሚያደርገው የተለመደ በጎ ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ የሕክምና ቁሳቁሱን የተረከቡ ሲሆን አየር መንገዱ ከበጎ-አድራጎት ድርጅቶች የተበረከተውን ድጋፍ በማጓጓዙ አመስግነዋል።

ከድርጅቶቹ የተበረከተው የሕክምና ቁሳቁስ የጤና ተቋማትን ለማስፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ 24 ኤር ባስ ኤ-350 አውሮፕላኖች እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም