በአፋር ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓት ቡድን በመከላከያ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓት ቡድን በመከላከያ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
ሠመራ ጥቅምት 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓት ቡድን በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አጥብቀው እንደሚያግዙ ገለጹ።
ፓርቲዎቹ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሠመራ ከተማ ዛሬ ባካሄዱት የምክክር መድረክ እንዳስታወቁት መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው ይገባል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአፋር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሴ አደን የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው የእብሪት ጥቃት ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉን በበላይነት ለመምራት ያለውን ፍላጎት በህዝብ ላይ ለመጫን የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።
ድርጊቱ የሀገርን ህልውና እና የህዝብን ሰላም አደጋ ላይ ለመጣል የተቃጣ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ተገዶ ወደ እርምጃ መግባቱን አውስተው የፖለቲካ ሃይሎች ከመንግስት ጋር ተቀናጀተን መስራት የሚገባን ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን በመረዳት የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ መላ አባላቶቻቸውን በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ተወካይ አቶ ሀንፈሬ መሃመድ ሉዋ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተካሄደው ፖለቲካዊ ሪፎርም ያልተመቸው የህወሓተ ሽብር ቡድን በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል ብለዋል።
አቶ ሀንፈሬ እንዳስረዱት መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በነበረው ቁርጠኝነት ችግሩን በሰለጠነ መንገድ በሆደ ሰፊነት በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም በጥፋት ቡድኑ ግትር አቋም ምክንያት የሰላም ጥረቱና ሙከራዎቹ ፍሬ አልባ ሆነዋል።
በተለይም የጥፋት ቡድኑ የሀገሪቱ የሉአላዊነት መገለጫና ብሄራዊ ኩራታችን በሆነው ሠራዊታችን ላይ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት የበድኑን የአሸባሪነትና የባንዳ ተግባር በግልጽ ያሳየ አሳፋሪ ድርጊት ነው ብለዋል።
ጥቃቱ መላ ኢትዩጵያውያን በተለይም ቆሜለታለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብን ጭምር የሚያሳፍርና የሀገሪቱን ታሪክ የሚያጠለሽ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት ከየትኛውም ብሄርና የፖለቲካ አመለካከት ነጻ ሆኖ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የህዝብን ሰላም ያስከበረ የሀገር ኩራት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ተወካይ አቶ መሀመድ አወል ናቸው።
ከዚህ እውነት ባፈነገጠ መልኩ የጥፋት ቡድኑ የትግራይን ህዝብ ደህንነት ለዘመናት ሲጠብቅ በቆየው ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከሀገር ክህደት የተለየ አይደለም ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀው እንደሚያወግዙና የህወሓትን ቡድን ስርዓት ለማሲያዝ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በመውጣት መረሃ ግብራቸውን አጠናቀዋል።