በነዋሪዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ጥቃት ያደረሱ 24 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተደመሰሱ - ኢዜአ አማርኛ
በነዋሪዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ጥቃት ያደረሱ 24 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተደመሰሱ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2013 (ኢዜአ) በህወሓት የጥፋት ቡድን ደጋፊነት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋኦ ቃንቃ አካባቢ በንጹሀን ነዋሪዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ጥቃት ያደረሱ 24 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተደመሰሱ።
ሌሎች 26 የኦነግ ሸኔ አባላት ሲማረኩ ተጨማሪ 23 አባላትም እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ለጸጥታ ኃይል መስጠታቸው ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የኦነግ ሸኔ ቡድን በፈጠረው የሽብር ተግባር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የንጹሀን ዜጎች ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙ የሚታወስ ነው ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ ማርዳሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ይህን እኩይ ተግባር በፈጸመው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
በዚህም በተለይ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋኦ ቃንቃ አካባቢ በኦነግ ሸኔ እና በህወሓት ደጋፊነት በነዋሪዎች ለይ የተወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ አሳዛኝ እንደነበር አስታውሰዋል።
የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱ በተፈጸመበት አካባቢ በተለያዩ አቅጣጫዎች ክትትል ሲያደግ ቆይቶ በወሰደው እርምጃ እስካሁን ወደ 24 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን አስታውቀዋል።
ሌሎች 26 የኦነግ ሸኔ አባላት ሲማረኩ ተጨማሪ 23 አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለጸጥታ ኃይል መስጠታቸውን ኮሚሺነሩ አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሺነር አራርሳ ገለጻ ከጥፋት ኃይሉ ኦነግ ሸኔ ቡድን ጋር በመሆን እርምጃ የሚወስዱ፣ ህዝቡን የሚዘርፉ እና ቤት የሚያቃጥሉ 74 የጥፋት ኃይሎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በእርምጃው የተለያዩ 24 የጦር መሳሪያዎች እና 289 ጥይቶችን ፖሊስ ከአጥፊው ቡድን እጅ ማስጣሉን አክለዋል።
''በአሁኑ ወቅት ይህ የአጥፊ ቡድን ሌሎች እርምጃዎችን እንወስዳለን በሚል ህዝቡን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ እያሸበረ ነው'' ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ህዝቡ እራሱንና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
"ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላትና ከፖሊስ ጋር በመሆን ይህን የአጥፊ ቡድን ሊከላከልና ሊያጠፋ ይገባል" ሰሉም አክለዋል።