በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ሀሰተኛ የብር ኖቶች ሲያዘዋውር የተገኙ 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ሀሰተኛ የብር ኖቶች ሲያዘዋውር የተገኙ 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መተማ/ ጎንደር/ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አዲሱንና ነባሩን ሃሰተኛ የብር ኖቶችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ አዲሱን ሃሰተኛ የብር ኖቶች ሲያዘዋውር የተገኘ አንድ ግለሰብ ይገኝበታል
ግለሰቡ በወረዳው ገለጎ ከተማ ሃሰተኛ የሆኑ 54 ሺህ 600 አዲሱን ባለ 200 ብር ኖቶችን ሲያዘዋውር መገኘቱን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሲሳይ ታደለ ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለውም ትናንት ቀን አምስት ሰዓት አካባቢ በገለጎ ከተማ በሚገኘው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ወደ ቁጠባ ሂሳቡ ለማስገባት ሲሞክር በባንክ ሰራተኞች ፍተሻ ስለተደረሰበት መሆኑን አስረድተዋል።
ግለሰቡ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዋሳኝ ወረዳ ከሆነው አለፋ ወረዳ እንደመጣ በምርመራ መረጋገጡን ጠቅሰው፤ሃሰተኛ ገንዘቡንም የቁም እንስሳት ሽጦ ከሌላ ግለሰብ እንደተቀበለ ለፖሊስ በሰጠው ቃለ መግለጹን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።
ወቅቱ የሰሊጥ ግብይት የሚፈፀምበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ግብይት በሚፈፅምበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ በዞኑ ገንዳ ውሃ ከተማ የድሮውን ባለ100 ሃሰተኛ የብር ኖት ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ተጠርጣሪ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብራራው የኋላ ገልጸዋል።
ተጠርጣሪው ከሱቅ የባለ 100 ብር የተንቀሳቃሽ ስልክ ካርድ ገዝቶ ሲሰጥ ባለሱቋ ሃሰተኛ መሆኑን ስትነግረው ትክክለኛውን ቀይሮ እንደሰጣት ለፖሊስ በጠቆመችው መሰረት በተደረገ ክትትል ከኪሱ 400 እና አልጋ ከያዘበት ክፍል ደግሞ ተጨማሪ አራት ሺህ 300 የድሮው ሃሰተኛ የብር ኖቶች ይዞ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አምባጊዮርጊስ ከተማ ህገ-ወጥ ግብይት የተፈጸመበት 38 ሺህ 600 ብር ሃሰተኛ ባለ 200 አዲስ የብር ኖቶች በቁጥጥር ሰር መዋሉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወንዶሰን ጥጋቡ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
በሃሰተኛ የብር ኖቶቹ ህገ-ወጥ ግብይት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 3 ግለሰቦች ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉም ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሃሰተኛ የብር ኖቶቹ የእርድ እንስሳት ግብይት ከፈጸሙ በኋላ አንደኛው ግብይት የፈጸመበትን ሃሰተኛ የብር ኖት ወደ ባንክ ለማስገባት ሙከራ ሲያደርግ ነው፡፡
ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር በማዋል የሃሰተኛ የብር ኖቶቹ ምንጭ ለማጣራት ምርመራ እንደ ጀመረም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ሁለት ግለሰቦች ከዘጠኝ ሺህ 800 ብር በላይ ባለ አንድ መቶ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ይዘው ግብይት ሲፈጽሙ ተገኝተው በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተመልክቷል።