የመንግስት ሠራተኞችን የጤና መድህን ስረአት ተጠቃሚ ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ሠራተኞችን የጤና መድህን ስረአት ተጠቃሚ ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) የመንግስት ሠራተኞችን የጤና መድህን ስራአት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ።
ፍኖተ ካርታው ሲዘጋጅ በመላ አገሪቱ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያንና የኑሮ ሁኔታን በማነጻጸር የተካሄደ ጥናትን መሰረት ማድረጉም ተመልክቷል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት መደበኛ ባልሆኑ ሥራዎች የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርአት ተቀርጾ በስፋት እየተራበት ነው።
መደበኛ በሆኑ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች አገልግሎቱን በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ የተዘጋጀው የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት በአዋጅና በደንብ ቢጸድቅም በሥራ ላይ እየዋለ አይደለም።
አገልግሎቱን ለመስጠት በመንግስት ሠራተኛው ዘንድ ከአከፋፈልና ከአገልግሎት ደረጃ ጋር በተያያዘ የተነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
" በዚህም የተነሱ ሃሳቦችን ከግምት በማስገባት አገልግሎቱን በአዲስ መልክ ለመጀመር የተደራጀ ምላሽ መስጠት በማስፈለጉ አገልግሎቱ ሳይጀመር ዘግይቷል" ብለዋል ዳይሬክተሯ።
በእዚህም በቀረቡ ቅሬታዎች መሰረት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያና የኑሮ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጥናት መካሄዱን ነው የገለጹት።
በጥናቱ መሰረትም በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች የሚከፈላቸው የደመወዝ መጠንና የየአካባቢው የኑሮ ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ ለጤና መድህን ሽፋን የሚቆረጠው ክፍያ ተመጣጣኝ እንደማይሆን ጥናቱ አመላክቷል።
"በተጨማሪም አዋጁን፣ ደንቡንና መመሪያውን ማሻሻል የሚያስፈልግበት አግባብ መኖሩንም በጥናቱ መገንዘብ ተችሏል" ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።
በቀጣይ ጥናቱን በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ አስፈላጊው ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ፍሬህይወት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑና ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የጤና እክሎች እየተበራከቱና የሚጠይቁት ክፍያም በዚያው ልክ ቀላል የማይባል በመሆኑ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኙ የማድረጉ ሥራ በስፋት ይሰራል።
በተለይም የመንግስት ሠራተኛው ኑሮው በጫና ውስጥ ያለ በመሆኑ የጤና አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት እንዳለበት ነው የተናገሩት።
"የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እንዲሰጥ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል ዳይሬክተሯ።
በዚህም እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ የመንግስት ሠራተኛውን ጨምሮ ሁሉምም ዜጋ የጤና መድን ሽፋን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።