በትግራይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል -- የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል -- የፌዴሬሽን ምክር ቤት
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 /2013 (ኢዜአ) “በትግራይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አግባብነት ካላቸው መንግስታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል” ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ መንግስቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡
“የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤ ሕግና ሥርዓት መተግበሩን ያረጋግጣል፤ አግባብ ባለው ህግ መሰረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤ የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤ እንዲሁም በፌዴራል መንግስቱ የሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል” ሲል ምክር ቤቱ ወስኗል።
ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ የሰጠው ምክር ቤቱ፤ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል” ብሏል።
የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትርሩ እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርቡም ውሳኔ አሳልፏል።
“ መላው የትግራይ ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ሕገወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገመንግስታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግስት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም ” የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን አቅርቧል።
መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ አላማ ይዘው እርስ በርስ በማጋጨት አገሪቱን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሰሩ ሀይሎችን ነቅተው እንዲጠብቁ አሳስቧል።
“ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም” በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን አቅርቧል።