የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው ሠላም ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው ሠላም ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ
ሀዋሳ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ ) በሲዳማ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው ሠላም መጠበቅ ዘብ እንዲቆሙ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጥሪ አቀረቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር መክረዋል።
በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሕወሃት ባለፉት 27 ዓመታት በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚ አሻጥር በፈጸመው ግፍ በህዝብ ተጠልቶና ተገፍቶ ከስልጣን ተሰናብቷል።
ይህም የህዝቦችን ህብረ-ብሄራዊ፣ አንድነትና ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ የለውጥ ምዕራፍ መከፈቱን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ጽንፈኛው የህወሐት ቡድን ሠላማዊ አካሄድንና በጋራ መጓዝን ባለመምረጥ የጥፋት መንገድ በመከተል አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጽም ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዚሁ ሂደት መንግስትን በማዳከም በህገ-ወጥ መንገድ ያጣውን ሥልጣን መልሶ ለመቆናጠጥ እየተፍጨረጨረ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ይህን ሁሉ ሂደት መንግስት በልበ ሰፊነት ስመለከተው የቆየበት አካሄድ የልብ ልብ ተሰምቶት ከሶስት ቀናት በፊት በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ትንኮሳ ፈጽሟል ብለዋል።
ይህ አካሄድ አደገኛና የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ መንግስት ህጋዊ ርምጃ መውስድ መጀመሩን አስረድተዋል።
ጽንፈኛው ቡድን የክልሉን ህዝብ መሸሸጊያ ለማድረግ ቢሞክርም የትግራይ ህዝብ በስሙ የተነገደበት፣ የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ያልተመለሰላቸው ሠላማዊ ህዝብ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
የፌዴራል መንግስትና የሃገር መከላከያ ሠራዊት ወገን የሆነው የትግራይን ህዝብ በማይጎዳ መልኩ አደጋውን ለመመከት ጥንቃቄ በተሞላ አካሄድ እየመራ ይገኛል።
ሴሬኛው ቡድን ግጭቱን በሰሜን በኩል የቀሰቀሰ ቢመስልም ሃገሪቱ ሠላም የሌላት ለማስመሰል ዓላማውን የሚያራምዱ ቡድኖችና ግለሰቦች ሊያሰማራ እንደሚችል ገልጸው እያንዳንዱ ነዋሪ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ለሠላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና እና መስኖ አማካሪ አቶ ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው በሃገሪቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣው የለውጥ ሂደት በህወሓት ዘመን የነበረውን መጠራጠር በማስወገድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሠላምና አንድነት አጎናጽፏል ብለዋል።
ለውጡ በአግባቡ መሬት እንዳይረግጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች ያልተጠበቁ ግፎች ሲፈጽሙ እንደነበር ገልጸዋል።
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ ያድርግ እንጂ ለህዝቡ ምንም ያልፈየደ ጸረ-ዲሞክራሲ መሆኑን የትግራይ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።
መንግስት ለትግራይ ህዝብ በማሰብ ሲታገሳቸው የቆየ ቢሆንም አሁን በመከላከያ ላይ ያካሄዱት ጥቃት ጭካኔ በመሆኑ ማስቆም ይገባል ብለዋል።
ይህ ሴሬኛ ቡድን የሃገርን ሠላም ለማደፍረስ ሊሠራ ስለሚችል ህብረተሰቡ አካባቢውን በጥንቃቄ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በህወሐት አገዛዝ ህዝቡ በመማረሩ ስልጠኑ አብቅቶለት አቃፊ የሆነ የለውጡ ሂደት መጀመሩን የገለጹት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ናቸው።
የሞከራቸው መስመሮች ሁሉ ሳይሳኩለት ሲቀር ባልታሰበ መልኩ በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የሃገር ክህደት ነው ብለዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዓለም ተስፋዬ መንግስት በጽንፈኛው ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
በከተማ ውስጥ በሚኖሩባቸው መንደሮች የዚህ ቡድን ርዝራዦች ሠላማቸውን እንዳያውኩ ለማጋለጥ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ኢሳያስ ዳለ በበኩላቸው ለህዝብና ለሃገር ሉዓላዊነት በየሜዳውና ዱር ሲዋደቁ በነበረ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ዕብደት ነው ብለዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም የዚህን ክፉ ቡድን ዓላማ ማክሸፍ እንዳለበት አመልክተዋል።