በስግብግቡ ጁንታ ህወሓት ላይ የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ኦፕሬሽን በስኬት ተከናውኗል... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በስግብግቡ ጁንታ ህወሓት ላይ የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ኦፕሬሽን በስኬት ተከናውኗል... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ)"በስግብግቡ ጁንታ ህወሓት" ቡድን ላይ የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ኦፕሬሽን በስኬት መከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ "በህገ ወጡ የህወሃት ቡድን" ላይ በተመረጡ አካባቢዎች የአየር ላይ ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
"በመጀመሪያው የኦፕሬሽን ግብ የመከላከያ ሃይላችን ከህወሓት ሃይል የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል" ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሎጅስቲኮችና ሌሎች የጦር ካምፖችን ሙሉ ለሙሉ ከጠላት ስጋት ነጻ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።
የመከላከያ ሃይሉ አሁን ላይ ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን ገልጸው የኦፕሬሽን ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዳንሻ አካባቢ ጠላት ሙሉ ለሙሉ የተደመሰሰ ሲሆን አካባቢውንም መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
የአየር ኃይል በወሰደው እርምጃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የነበሩ ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደም መቻሉንም ገልፀዋል።
"የህወሃት ጁንታ" እነዚህን መሳሪያዎች በመያዝ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀስ እንደነበረም ነው ያስረዱት።
"በወንጀለኛው ቡድን" እስከ 300 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ሮኬቶችን የመጠቀም ፍላጎት በመኖሩ በመቀሌና አካባቢው የከባድ መሣሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ላይ ጥቃት ተፈፅሞበታል ብለዋል።
በዚህም የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ኦፕሬሽን በስኬት መከናወኑን ተናግረዋል።
የአየርም ሆነ የምድር ላይ ጥቃቱ ሰላማዊ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ሁሉ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በህወሓት ተገዶ ወደ ውጊያ የገባው የክልሉ ልዩ ሃይልም ለመከላከያ ሰራዊት በሰላም እጁን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።