ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራን እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ)  የኢፌዴሪ መንግስት ህግ መንግስትን በመጣስ በህወሃት ቡድን እየተፈፀመ ላለው የማያባራ ጠብና ምላሽ ውጤታማ ህግን የማስከበር እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ለሊት አካባቢ በህወሃት የተሞከረው የብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ አስቀድሞ የታቀደውን እና ድንገተኛ ጥቃቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በፌደራል ስልጣን እና ሃላፊነት በክልሉ ውስጥ መጠነ ሰፊ የህግ ማስከበር ዘመቻ በአንቀጽ 51 መሰረት ተጀምሯል ብሏል ጽህፈት ቤቱ።

አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ አገሪቱን በጭቆና ለ27 ዓመታት ሲገዛ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ሰላማዊ ዜጎችን እንደ ጋሻ በመጠቀም በመቐለ ከተማ ከፍትሕ ሸሽቶ መቆየቱን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡

ቡድኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተለያዩ ቡድኖች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አገርን የማተራመስ ተግባር ላይ ተጠምዶ የነበረው ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን በትዕግስት ሲከታተል መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል መንግስቱ ህወሃት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የሪፎርም አካል እንዲሆን የውይይት፣ የድርድርና የጋራ መግባባት እድሎች ተከፍተው ሁሉም የሰላም አማራጮችን የተጠቀመ ቢሆንም ቡድኑ ባሳማራቸው የጥፋት ኃይሎችአማካኝነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

ለዚህም ተግባሩም በምዕራብ ጎንደር፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጉራ ፈርዳ፣ እንዲሁም በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ጥቃት መፈጸሙን በማስታወስ።መንግስት በገለልተኛ አካላት በኩል ድርድር እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ህወሃት ሕገ ወጥ ምርጫ በማድረግና የፌዴራል መንግስቱን እንደ ሕገ ወጥ አካል በመቁጠር ለፌዴራል መንግስቱ እውቅና እንደማይሰጥ ገልጸ ነበርም ተብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የፌዴራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ራሱን እንዲከላከል እንዲሁም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ትእዛዝ ማስተላለፉን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስፈንና የማስጠበቅ፣ ህገ-መንግስቱን መጠበቅ መከላከል እና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባሩን በትግራይ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ሰላም የማረጋገጥ ተግባሩን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ 6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል ግብረ ሀይሉ መቋቋሙንና የሚያከናውናቸው ተግባራትም መዘርዘራቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ይህንን ተከትሎም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን እና የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁን ማጽደቁን አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

ግብረ ሀይሉ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜም፦

• ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውንም የፀጥታ ሃይል ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ•

• የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ጨምሮ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መጣል

• የሰአት እላፊ ገደብ የማውጣት

• የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም

• የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ የማድረግ

• ህገ ወጥ በሆነ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የመያዝና የማቆየት ኃላፊነት ይኖረዋል።

የፌደራል መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ህገ መንግስቱን የመጠበቅ እና መከላከል እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም መግለጫው አስታውቋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም በትግራይ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የእነዚህን ወንጀለኞች ቡድን ተግባር ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስቆሙም በመግለጫው ተመላክቷል።

838313 SharesLikeCommentShare

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም