ጎረቤት አገሮች "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል በጋራ እየሰራን ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ጎረቤት አገሮች "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል በጋራ እየሰራን ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) ጎረቤት አገሮች "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል በጋራ እየሰሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉት የሶስትዮሽ ድርድርም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን እንደሚፈታ ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም በግድቡ ላይ ያለውን የሶስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍት እንዳሉት ባሉፉት ሁለት ሳምንታት ከህንድ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና አረብ ኢምሬትስ ጋር በሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።
ጎረቤት አገሮች "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
በሁሉም እርከን ላይ ካሉ የሱዳን አመራር አባላት ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የጅቡቲ መንግስት፤ የኢትዮጵያ ሰላም የሁላችንም ሰላም ነው የሚል አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ ህወሃት በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጥቃት በማውገዝ የሰጡት መግለጫም ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን መረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የህወሃት ቡድን ጋር ተገዶ የገባበትን ጦርነት በተመለከተም ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች አስረድቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በተከተሰተው ውስጣዊ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም "ልትቀይር ትችላለች" ማለትም ስህተት መሆኑን ገልጸዋል
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሚያደርጉት ድርድር "ወሰድ መለስ" የሚያደርገው ድርድር መሆኑንም ገለጸዋል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።
ኢትዮጵያ "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፈታት አለበት" የሚል የቆየ አቋም አላት ያሉት አምባሳደር ዲና በቀጣይም የአፍሪካ ህብረት ውጤት ላይ እንደሚደርስ እናምናለን ብለዋል።