የአገርን ሰላም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሆን ይገባዋል- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ - ኢዜአ አማርኛ
የአገርን ሰላም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሆን ይገባዋል- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) የሀገርን ሰላም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ።
በትግራይ ክልል ህወሃት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱና በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም መንቀሳቀሱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢዜአ በሰጡት ሃሳብ፣ ድርጊቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
በፌዴራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መካከል የነበረውን ቅራኔ ለበርካታ ጊዜያት በውይይት እንዲፈቱ ምክረ-ሃሳብ በመስጠት ሲሳተፉ እንደቆዩ አንስተዋል።
''ነገር ግን የማዕከላዊ መንግስት በበዛ ትዕግስት ነገሮችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የሄደበት መንገድ ስልጣን በተጠሙ የህወሃት አኩራፊዎች ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ቆይቷል'' ብለዋል።
"መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሲል ለህወሃት አመራሮች ያሳየው ሆደ ሰፊነትና ትዕግስት የሚደነቅ ነው በማለት፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከልክ ያለፈውን አካሄድ ለማስቆም እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ ነው" ብለዋል።
''የትግራይ ህዝብ ሳይወድ በግድ በህወሃት አገዛዝ ስር እንዲቆይ እየተደረገ ነው ሲሉ አክለዋል።
አገርን በእልህ መምራት የማይታሰብ መሆኑንም በመግለጽ ''ግርግር የሚያነሳ አፍንጫውን ተመትቶ ራሱ ይጎዳል እንጂ አቧራ በተነሳ ቁጥር የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ላይ የሚወድቅ አይሆንም'' ብለዋል።
በየትኛውም አካባቢ ያለ ኢትዮጵያዊ የአገሩን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸው፤ የአገርን ሰላም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሆን ይገባዋል ብለዋል።
ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ከሆነ የትኛውም ኃይል ችግር መፍጠር አይችልም ሲሉም አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እየሆነ ላለው ነገር የህወሃት አመራሮች ቀጥተኛ ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጸው፤ ህዝብ የሚከተለው መሪ የህዝቡ ምሳሌ እንጂ የጥፋት መንገድ ጠቋሚ መሆን የለበትም ብለዋል።