ቀጥታ፡

ብሔራዊ ፓርኮችን ከአደጋ ለመከላከል እየተሰራ ነው -- የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን

ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

 በኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮች  ይገኛሉ።

ህገወጥ ሰፈራና አደን፣ ድርቅና ሰደድ እሳት በፓርኮቹ ላይ ጉዳት በማድረስ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ መሆናቸው  ተመልክቷል።

በፓርኮች ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን ችግሮች ለመከላከል  ባለስልጣኑ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች መዘጋጀታቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን  ተናግረዋል።

ከእሳት አደጋ ጋር ተያይዞ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል  የሚያግዝ  የስልጠና መሳሪያዎች  ድጋፍ ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/  መገኘቱን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

ፓርኮቹ ያሉባቸውን  የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለማቃለል  ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህ ላይ መንግስት ከሚያከናውናቸው ስራዎች በተጨማሪ ባለሀብቶችን በዘርፉ ለማሳተፍ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው ፤ በቅርቡ የሱዳን ባለሀብቶች መጥተው ፓርኮቹን እንደጎበኙም ጠቅሰዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ  በፓርኮቹ አካባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ ሀብቱን እየተንከባከበ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ስራዎች ላይ  ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸው እንደ መልካም አጋጣሚ እንጠቀምበታለን ብለዋል።

በዚህም መሰረታዊ ችግሮቹ ተወግደው አገሪቱ ከዘርፉ  የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮች እንዳሏት ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም