የህወሓትን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ለማክሸፍ ህዝቡ ከፀጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓትን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ለማክሸፍ ህዝቡ ከፀጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ
መተማ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) የህወሓት የጥፋት ቡድን ይዞ የተነሳቸውን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ለማክሸፍ ህዝቡ ከመንግስት እና የፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጠየቁ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ የምዕራብ ጎንደር ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ጋር የሚዋሰን የልማት ቀጠና ነው ብለዋል።
የህወሓት አጥፊው ቡድን የኢትዮጵያ ህዝቦች እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እና አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በማድረግ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን፣ አካልና ንብረታቸውን እንዲያጡ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያውያን ብሎም የመላው አፍሪካ ኩራትና ክብር በሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ትንኮሳ በማድረግ የሃገርን ሉአላዊነት ቡድኑ መድፈሩን ጠቅሰዋል።
በለውጥ ሃይሉ ተገፍቶ ስልጣን የለቀቀው ቡድን ሃገርን የማፍረስ የመጨረሻ ተልእኮ ይዞ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል።
ሆኖም የጥፋት ሃይሉ የጀመረው ድፍረት የተሞላበት ትንኮሳ የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱ እንዲፈጸም የሚያደርገው መሆኑን ገልጸዋል።
"የዞኑ ህዝብ የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበር የሀገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ የድል ተጋድሎ ታሪክ ያለው ነው" › ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የቡድኑ ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ለማክሸፍ ከመንግሥትና ፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኀብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የጥፋት ቡድኑ በሁሉም አካባቢ ባሉ የእምነትና የገንዘብ ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ አሸባሪ ሃይሎችን እንዳሰማራ መረጃ መኖሩን ጠቁመው ለተቋማቱ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ኀብረተሰቡ በአካባቢው ፀጉረ ልውጥና አጠራጣሪ ሁኔታ ካየ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡