የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክር ተገጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክር ተገጸ
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴው ግድብ ላይ በቅርቡ የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያዊያን ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክረው ተገጸ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ንግግር አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ ጥረትና በህዝቦቿ ተሳትፎ በሉዓላዊ ግዛቷ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገነባት ከጀመረች ዘጠኝ ዓመት ማሳለፏ ይታወቃል።
ከዓባይ ውሃ በረከት ለመቋደስና የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ላይ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብና ከስምምነት ለመድረስ በራሳቸውና በተለያዩ አካላት አሸማጋይነት ሲደራደሩና ሲወያዩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ምንም እንኳን አንዳች መቋጫ ላይ ባይደርሱም።
በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት ለመድረስም ግብጽ በያዘችው ግትር የ"ብቻዬን ልጠቀም" ፍላጎት በየጊዜው ሲካሄዱ የቆዩት ድርድሮች ሁሉ ከግብ ሳይደርሱ ቀርተዋል፡፡
በራሷ ጥረትና በህዝቦቿ ተሳትፎ ያላትን ጸጋ ተጠቅማ ድህነትን ለማሸነፍ የምትጣጣር አገርን ታላቅ ፕሮጀክትን አስመልክቶ የአሜሪካው ፕሬዚዳትን ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በቅርቡ "ግብጽ ግድቡን ታፈነዳዋለች፤ አሜሪካም ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ከልክላለች" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የፕሬዚዳንቱ ንግግር የልእለ ኃያሏን አገር ህዝቦችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቋም ያንጸባርቃል ማለት ቢያስቸግርም ከአገር ቤት እስከ የተለያዩ ክፍለዓተ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም ፍትህ ፈላጊ ተቋማትና ግለሰቦችን ያሳዘነ ክስተት ነበር፡፡
ከዚህ በመነሳትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያደረጉት ንግግር በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የፈጠረውን ስሜት እና ያለውን አንድምታ ለመገምገም በበይነ መረብ ጥናት አካሂዷል፡፡
የፕሬዚደንቱ ንግግር በህዝቡ ዘንድ ምን ፈጠረ? እንድምታዎቹስ? ምንስ ትምህርት ይሰጣል? የሚሉትን በማካተት ለአራት ቀናት የቆዩ ጥያቄዎች ለአስተያየት ሰጪዎች ክፍት ሆነው ቆይተዋል፡፡
በጥናቱ በአዲስ አባበ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ፣ በሶማሌ ፣ በአፋር ፣ ቤንሻንጉልና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን ጭምር ምላሽ በመስጠት ተሳትፈዋል።
ከጥናቱ ተሳታፊዎች 79 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች የፕሬዚደንቱ ንግግር ህዝቡ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚረዳ ነው የገለጹት።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ግድቡን ለማጠናቀቅ በአገራዊ አንድነት ከመግባባት ላይ በመድረስ እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድነት መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ከሰጡት 71 ነጥብ 8 በመቶዎቹ ደግሞ ህዝቡ በአንድነት ቆሞ አገራዊ አንድነቱን ለማጠናከር የፕሬዚዳንቱ ንግግር አበርክቶው ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል፡፡
"ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ስለሰጡ ስላልሰጡ አገራዊ አንድነት አይመጣም" ያሉት ከፊል አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ በውስጥ ያሉ ችግሮችን በአግባቡ በመፍታት ከመግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
ሌሎች 82 ነጥብ 1 በመቶ በሚሆኑት ተሳታፊዎች ንግግሩ ከፍተኛ ቁጭት እንደፈጠረ ገልጸዋል።
ለእዚህም ከግብጽ ጋር በር ዘግተው ሲወያዩ የነበረውን ፕሬዚዳንቱ ይፋ ማድረጋቸው እንዲሁም የአሜሪካና ግብጽ ግንኙነት የታወቅ መሆኑ የሚሉትና ሌሎችንም ምክንያቶች አስቀምጠዋል፡፡
በጥናቱ ከተሳተፉት 59 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ከግድቡ ጋር በተያያዘ ተጨባጭ የደህንነት ስጋት ይፈጥራል የሚል እምነት እንደሌላቸው መልሰዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያላቸውን ልዩነት በማጥበብ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ የአገራቸውን ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለባቸው ነው የመከሩት።
አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ተቋማትና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የሰጡት ድጋፍና አለኝታነትም ሚደነቅና ከፍተኛ መሆኑን የጥናቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡