ቀጥታ፡

ጎረቤት አገራት "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) ጎረቤት አገራት "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል እየሰሩ መሆኑን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉት የሶስትዮሽ ድርድርም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን እንደሚፈታ ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም የሶስትዮሽ ድርድሩን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከህንድ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና አረብ ኢምሬቶች ጋር በሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ምክክር መደረጉን አንስተዋል።

በሁሉም እርከን ላይ ካሉ የሱዳን አመራር አባላት ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን ያሉት ቃል አቀባዩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

የጎረቤት ሀገራት "የኢትዮጵያ ደህንነት የእኛም ደህንነት ነው" በሚል እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የጅቡቲ መንግስት የኢትዮጵያ ሰላም የሁላችንም ሰላም ነው የሚል አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።  

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ ህወሃት በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ማውገዛቸውንም አምባሳደር ዲና አስታውሰዋል።

መንግስት ከፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ጋር ተገዶ የገባበትን ጦርነት በተመለከተም ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች አስረድቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተከሰተው ውስጣዊ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም "ልትቀይር ትችላለች" ማለትም ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሚያደርጉት ድርድር "ወሰድ መለስ" የሚያደርገው ድርድር መሆኑንም ገልጸዋል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።

ሶስቱ አገራት በሞዳሊቲ ላይ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን ስምምነት ላይ ቢደርሱም ግብጽ ግን አስካሁን አልተቀበለችውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፈታት አለበት" የሚል የቆየ አቋም አላት ያሉት አምባሳደር ዲና በቀጣይም የአፍሪካ ህብረት ውጤት ላይ እንደሚደርስ እናምናለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም