ቀጥታ፡

የህወሓት አጥፊ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት እናወግዛለን-የጋምቤላ ነዋሪዎች

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 27 /2013 (ኢዜአ) የህወሓት አጥፊ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት እናወግዛለን ሲሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።


ዳር ድንበርና ሰላምን ከመጠበቅ ባለፈ በልማት ሥራዎች የህዝብ አጋር በሆነው ሰራዊት ላይ የጥፋት ኃይሉ የፈጸመው ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን ነዋሪዎቹ  ለኢዜአ ተናግረዋል።

አቶ አቡላ ኡጀር በሰጡት አስተያየት የህወሀት ቡድን የህዝብ አጋር በሆነው ሰራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት የሚያሳዝን ተግባር ነው።

”የሀገርን ድንበርና ሰላም እየጠበቁ በነበሩ ልጆቻችን ላይ አሳፊሪ ድርጊት በፈጸመው ቡድን ላይ አስፈላጊው እርምጃ  ሊወሰድ ይገባል” ብለዋል።

ህወሓት በሚያሰማራቸው የጥፋት ቡድኖች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በአካባቢያቸው እንዳይከሰት ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

"የህወሓት የጥፋት ቡድን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ለዘመናት አብሮ የቆየውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማጋጨትና ተላላኪዎቹን በማሰማራት የበርካታ ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ እያደረገ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ደረጀ ሙረዳ ናቸው።

በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ምንም በማያውቁ ዜጎች ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮውን በመቀጠል በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት የሚያሳፍር ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

"የጥፋት ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

ህወሓት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጥፋት ኃይሎችን በማደራጀትና ከመሰሎቹ ጋር በመቀናጀት የሚፈፅማቸውን እኩይ ድርጊቶች ለማክሸፍ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኮንግ ጆክ ናቸው።

የጥፋት ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው እኩይ ተግባር አሳፋሪ መሆኑን በመግለፅ መንግስት የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም