ጂፕሰምን እንደ ግንባታ ግብዓት በስፋት ለመጠቀም እየተሰራ ነው-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጂፕሰምን እንደ ግንባታ ግብዓት በስፋት ለመጠቀም እየተሰራ ነው-ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) የጂፕሰም ምርትን ለግንባታ ግብዓትነት በስፋት ለማዋል በዘርፉ ከተሰማሩ ፋብሪካዎች ጋር እየሰራ መሆኑን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱዩት አስታወቀ።
ኢንስቲቱዩቱ ከዮናታን ቢቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር የምርት ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር የውይይት ፕሮግራም ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በፕሮግራሙ አዲስ ኤም ጂ ልስን (ፕራይም ኮት) የተሰኘ ምርት ተዋውቋል።
በኢንስቲትዩቱ የሲሚንቶና ተዛማጅ ኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ልማት ዳይሬክተር አቶ ስመኝ ደጉ እንደተናገሩት ምርቱ ጂፕሰም በግንባታው ዘርፍ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ አስተዋጽኦ አለው።
በዚህም ለልስን አገልግሎት የሚውለውን የሲሚንቶን ፍላጎት በ35 በመቶ ለመቀነስ በዘርፉ ከተሰማሩ ፋብሪካዎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጂፕሰም ከሲሚንቶ ጋር ሲነጻጸር የግድግዳም ሆነ የኮርኒስ ልስን ወጪን ከ30-40 በመቶ እንደሚቀንስም አቶ ስመኝ አመልክተዋል።
በጂፕሰም የተሰራ ግንባታ የውሃ ፍጆታው አነስተኛ፣ፈጥኖ የሚደርቅና ቀለም ለመቀባት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
እንዲሁም የህንጻውን ክብደት በመቀነስ ረዥም ዕድሜ እንዲኖረው ከማድረጉም በላይ፤ ቀለም በጥሩ ሁኔታ እንዲይዝና ለዓይን ማራኪ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚቀላቀሉ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
በዮናታን ቢቲ.ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አማካሪ ኢንጂነር ሰለሞን ይርጋ በበኩላቸው አዲሱ ምርት በሲሚንቶ ላይ የነበረውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ምርቱ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ ወደ ገበያ መግባቱንም አክለዋል።