የህዳሴ ግድብ መገንባት ለኢትዮጵያ እናቶች የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል - እናቶች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ መገንባት ለኢትዮጵያ እናቶች የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል - እናቶች
ጥቅምት 27/2013(ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት የኢትዮጵያ እናቶችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እናቶች ተናገሩ።
ግድቡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ቢበዛበትም የኢትዮጵያዊያን ሀብት በመሆኑ ግንባታው እንዳይስተጓጎል መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ በተለይም ኋላ ቀር ኑሮ ለሚገፉ እናቶች ትርጉሙ ብዙ ነው ብለዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጫልቱ አወል እንዳሉት የግድቡ መጠናቀቅ ወገባቸው በእንጨት ሸክም ለተጎዳው እናቶች የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
የኦሮሞ ባህል ማዕከል ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ምትኬ ቢተውልኝ በበኩላቸው ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ አገሬን፣ ኑሮዬን እለውጥበታለሁ ብሎ በራሱ ተነሳሽነት የሚገነባው መሆኑን ተናግረዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ በተለይም በብዙ የኑሮ ጫና ውስጥ ያሉ ሴቶችን ችግር ለማቅለል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፎዚያ መሐመድ የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነው የህዳሴ ግድብ እንደ ሴት ደግሞ ትርጉሙ ብዙ ነው ብለዋል።
የበለጸጉ አገራት የራሳቸውን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅመውና አልምተው የህዝባቸውን ኑሮ የተሻለ እንዳደረጉ አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በቁርጠኝነት ያጋመሱት ታላቁ የህዳሴ ግድብም ከዚህ ቁጭት በመነሳት የሚገነባ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ የላቀ ጥቅም በሚያስገኘው ግድብ የውጭ ጣልቃ ገብነት ቢበዛበትም በእልህ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ ከፍጻሜ ደርሶ እውን መሆኑ ዓይናቸው በጭስና ወገባቸው በእንጨት ሸክም ለተጎዱ የኢትዮጵያ እናቶች የተለየ ትርጉምና የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የግድቡ ግንባታ ለድርድር የማይቀርብና የኢትዮጵያዊያን ሀብት በመሆኑ ለፍጻሜ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት በመደገፍ እገዛቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።