የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በ2020 የኢንዶኔዥያ የንግድ ትርኢት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በ2020 የኢንዶኔዥያ የንግድ ትርኢት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ በአውሮፓዊያኑ 2020 በሚደረገው የኢንዶኔዥያ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።
የንግድ ትርኢቱን በማስመልከት በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ ኢምባሲና የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት በተደረገው የኢንዶኔዥያ የንግድ ትርኢትና ባዛር 22 የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
የዘንድሮው ደግሞ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በበይነ መረብ አማካኝነት በሚካሄደው የንግድ ትርኢትና ባዛር የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በበኩላቸው ኢንዶኔዥያ በበይነ መረብ አማካኝነት በምታካሂደው የንግድ ትርኢትና ባዛር የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ከፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
“በበይነ መረብ መደረጉ ብዛት ያላቸው የኢትዮጵያ ነጋዴዎች እንዲሳተፉ ያደርጋል” ነው ያሉት።
በ2020 የሚከናወነው የኢንዶኔዥያ የንግድ ትርኢትና ባዛር 35ኛው ነው።