የትግራይ ህዝብ የአገር ከሀዲዎችን በማጋለጥ ነጻነቱን ለማስመለስ ከመንግስት ጎን እንዲቆም የምክር ቤት አባላት ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ህዝብ የአገር ከሀዲዎችን በማጋለጥ ነጻነቱን ለማስመለስ ከመንግስት ጎን እንዲቆም የምክር ቤት አባላት ጠየቁ
አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ የአገር ከሀዲዎችን በማጋለጥ ነጻነቱን ለማስመለስ ከመንግስት ጎን እንዲቆም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የህወሓት አንጃ ያደራጀው ኃይል በሰሜን የአገር መከላከያ ሠራዊት እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት አገርና ህዝብን ለማዳን እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል መሆኑን የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
ከአባላቱ መካከል ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ በህወሓት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት "አሳዛኝና አሳፋሪ" ብለውታል።
የህወሓት አመራሮች አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ሲያጋጩ የኖሩና ኢትዮጵያ እንድትበተን ሳይታክቱ ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል ሰላምን ከማስከበር ባለፈ በርሃ ላይ ሆኖ ህዝቡን በቅንነትና በተማኝነት ሲያገለግል የነበረ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም የአረመኔነት ጥግ መሆኑንም ጨምረዋል።
የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድና ህዝብ አክባሪ መሆኑን ገልጸው "የህወሓት መሪዎች የአገር ፍቅር የሌላቸውና ባንዳዎች ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ከውስጡ አንቅሮ እንዲያወጣም ነው ወይዘሮ ብርቱካን የጠየቁት።
ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አስነዋሪ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጊቱን በክልሉ ባለው ጭቆና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ የትግራይ እናቶች፣ ወጣቶችና ሁሉም የህብረሰተብ ክፍል ሊያወግዘው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
"የህወሓት አመራሮች የትግራይ እናቶችን ኑሮ ማሻሻል ያልቻሉና በችግር ጊዜ ብቻ መሸሸጊያ እንዳደረጓቸው ህብረተሰቡ ተገንዘቦ ሊያወግዛቸው ይገባል" ብለዋል።
መንግስት በአሁኑ ወቅት ሰላምና ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ በበጎ ጎን እንደሚያዩት የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት ህዝቡም አካባቢውን በመጠበቅ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።