ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሎዛ አበራ እና ሰናይት ቦጋለን አስፈረመ

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ሎዛ አበራ እና ሰናይት ቦጋለን አስፈረሟል።

የሁለቱ የተጫዋቾች የፊርማ ስነ ስርዓት ዛሬ ከቀትር በኋላ ተካሄዷል።

ሎዛ አበራ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ጋር የአንድ ዓመት ውል የተፈራረመች ሲሆን በእዚህም 50 ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ ከማግኘት በተጨማሪ ፕሮፌሽናል ተጫዋች በመሆኗ ደግሞ በየወሩ 25 ሺህ ብር ጉርሻ ታገኛለች ተብሏል።

የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ወይም ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ከጨረሰችና ክለቧ የሊጉ አሸናፊ ከሆነ 100 ሺህ ጉርሻ የምታገኝ ይሆናል።

በተጨማሪም ሎዛ አበራ በውጭ የመጫወት እድል ካገኘች ከክለቡ ጋር ተነጋግራ መልቀቅ እንደምትችል በውሏ ላይ ተቀምጧል።

የአማካይ ክፍል ተጫዋቿ ሰናይት ቦጋለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ጋር የሁለት ዓመት ውል የፈረመች ሲሆን 49 ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ ታገኛለች።

ሎዛ አበራ ክለቡን የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ለማድረግ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግና ክለቧ የሊጉ አሸናፊ እንደሚሆንም እርግጠኛነቷን ገልጻለች።

"የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መልካም የውድድር ዘመን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።

ሰናይት ቦጋለ ክለቡን በመቀላቀሏ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ፣ ቡድኗን የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ለማድረግ ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች።

ሎዛ አበራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 7 ቁጥር ማሊያን የምትለብስ ሲሆን ሰናይት ቦጋለ ደግሞ 21 ቁጥር ማሊያን ለብሳ የምትጫወት ይሆናል።

ሎዛ አበራ በሃዋሳ ከተማ፣ ደደቢትና አዳማ ከተማ ተጫውታለች።

ከአገር ውስጥ ክለቦች በተጨማሪ የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በማልታ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ለሚገኘው ቢርኪርካራ ክለብ በመፈረም በ12 ጨዋታ 30 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ኮከብ አግቢ ሆና የጨረሰች ሲሆን ክለቧንም የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ ማድረጓ የሚታወስ ነው።

ሎዛ ከሁለት ዓመት በፊት በስዊዲኑ ኩንግስባካ ክለብ በነበራት የሙከራ ጊዜ በሰባት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስቆጠረች ሲሆን በዛው ዓመት ከክለቡ ጋር የስዊዲን ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆናለች።

በተጨማሪም የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ በቱርኩ አንላይስፖር ክለብም የሙከራ ጊዜ ማሳለፏ አይዘነጋም።

የአማካይ ተጫዋቿ ሰናይት ቦጋለ ከዚህ በፊት ለአዳማ ከተማና ለደደቢት የተጫወተች ሲሆን በ2011 ዓ.ም በስዊድኑ ክለብ አይኤፍኬ አማል የሙከራ ጊዜ ማሳለፏ የሚታወስ ነው።

በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 10 ክለቦች ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም