ቀጥታ፡

በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው- የክልል ሃይማኖት ተቋማት

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) ህወሓት በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ አሳፋሪ ድርጊት ነው ሲሉ የክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች አወገዙ።

ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሓት የጥቃትና የዘረፋ ጥቃት ማድረጉን የኢፌዴሪ መንግሥት ይፋ አድርጓል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤያት አመራሮችም ድርጊቱን የሚወገዝ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ እንደተፈጸመ የሚቆጠር አሳፋሪ ድርጊት ብለውታል።

የኦሮሚያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ  የአገር  መከላከያ ሰራዊት አባላት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የወከሉ ልጆች በመሆናቸው ጥቃቱ  የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሆነ ይናገራሉ።

የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርዱ ሰብሳቢ መልዓከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለምና የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ሰይድ መሐመድም ድርጊቱን አውግዘውታል።

አገርን ከውጭ ወረራና ጥቃት የሚታደግ፣ ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅና ሉዓላዊነት በሚያስከብርን ሰራዊት ላይ በራሱ ወንድሞች ጥቃት መፈፀሙ አሳዛኝ ድርጊት ብለውታል።

ጥቃቱም አገርና ሕዝብን የናቀ፣ አገርንን ያዋረደ በመሆኑ በአገርና ሕዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሼህ ሐጂ ከረር አልቃርብ፣ የድሬዳዋ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረውና የሐረሪ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ መጋቢ መስፍን በየነም አመራሮች

የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖተኛ፣ ጥበበኛ፣ ባለታሪክና የኢትዮጵያ መሰረት እንደሆነ የገለፁት የሃይማኖት አባቶች፣ ድርጊቱን የህወሓት ፖለቲከኞች እንጂ፤ ሕዝቡን እንደማይወክል ተናግረዋል።

በጦርነት ማንም አሸናፊ እንደማይሆን በመግለጽ፤ አሁንም ቢሆን ሁለቱም ወገኖች ወደሰላም እንዲመጡ ጠይቀዋል።

ለዚህም አስነዋሪ ተግባር የፈጸሙ ኃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሰላም እንዲመለሱ፣ ለሰላም ሂደቱም አባቶች፣ ምሁራንና ወጣቶች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም