በ19 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን ሁለት ቤተ ሙከራዎች አስመረቀ--ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በ19 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን ሁለት ቤተ ሙከራዎች አስመረቀ--ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት 19 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውን ሁለት ቤተ ሙከራዎችን አስመረቀ፡፡
ኢኒስቲትዩቱ 46 የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑንም ጠቁሟል፡፡
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ እንደተገለጸው ዛሬ የተመረቁት ሁለት ቤተሙከራዎች የማይክሮ አልጌ ባዮቴክኖሎጂ እና የኮቪድ-19 መመርመሪያ ቤተ ሙከራዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እንዳሉት የማይክሮ አልጌ ባዮቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ በኢትዮጵያ በስፋት የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከል የሚያስችል ነው፡፡
የማይክሮ አልጌን ዘር በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በህጻናት ላይ በስፋት የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ከመከላከል ባሻገር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታን ማመቻቸት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ቤተ ሙከራው የህጻናት አልሚ ምግቦችን ለማምረት የሚረዳ የማይክሮ አልጌን ዘር ለማውጣት እንደሚያስቸልም ነው ዶክተር ካሳሁን የተናገሩት፡፡
የአልጌ ዘር በቢሾፍቱ፣ በአብያታና ሻላ ሐይቆች ላይ በስፋት እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ በነዚህ አካባቢዎች ንጽህናው የጠበቀ ማይክሮ አልጌ ማምረት እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው የማይክሮ አልጌ ባዮቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ በ15 ቀን ውስጥ 100 ሊትር የማይክሮ አልጌ ዘር ማልማት የሚችል መሆኑንም ዶክተር ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በነበረው የኮቪድ-19 መመርመሪያ ቤተሙከራ ከ33ሺህ በላይ ናሙናዎችን መመርመር መቻሉን አስረድተው፣ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ቤተ ሙከራ ቀላል ምርመራዎችን ለማድረግና ምርምሮችን ለማካሄድ ከማስቻል ባለፈ ግብአቶችን ለማምረት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በኢኒስቲትዩቱ የኢንዱስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ፋንታሁን ወልደሰንበት በበኩላቸው ሁለቱ ቤተሙከራዎች አዲስ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በተለይ የማይክሮ አልጌ ባዮቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ በአገራችን የመጀመሪያው ቤተ ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለማይክሮ አልጌ ቤተ ሙከራ በ8 ሚሊዮን ብር ፤ ለኮቢድ-19 ምርመራና ምርምር ማድረጊያ ቤተ ሙከራ ደግሞ የ11 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት 46 የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን የጠቀሱት ዶክተር ፋንታሁን፣ የምርምር ስራዎቹን ለኢንተርፕራይዞች በመስጠት የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የተለያዩ ሥራዎች እተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ቤተ ሙከራዎቹን የመረቁት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ፎዚያ አሜን በበኩላቸው፣ በባዮቴክ ባለሙያዎችና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉ ምርምሮች አገሪቱ ለያዘቻቸው የእድገት አቅጣጫዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በየጊዜው የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች በተለይ የሴቶችን ድካም ከማቃለል ባሻገር ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲመረት በማድረግ በኩል ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፤
ሚኒስቴሩም ኢንስቲትዩቱ ለሚያከናውነው ተግባርና የምርምር ሥራ ለሚሰሩ ምሁራን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
በምረቃው ስነስርአት ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች በአውደርዕይ ቀርበው የተጎበኙ ሲሆን በባለሙያዎችም ገለጻ ተደርጎባቸዋል።