በህወሓት ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በህወሓት ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ
ደሴና ደብረ ብርሃን ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) በህወሓት በጥባጭ ቡድን ላይ የተጀመረው እርምጃ ድል እስኪገኝ ተጠናክሮ እንዲቀጠል የሚደግፉ መሆናቸውን በደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አራጌ ሰይድ እንደተናገሩት ህወሓት የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ አገር ከማተራመሱም ባለፈ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ደፍሯል፡፡
የአገር ኩራት በሆነው መከላከያ ሠራዊት የተፈፀመው የጥቃት ሙከራ በውጭ ጠላት ያልተደረገ አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በመንግስት የተጀመረው እርምጃም ድል እስኪገኝ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡን አስተባብረው ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አባይ አበራ በበኩላቸው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ህገ ወጥ ተግባር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን የሚቆምበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
ህወሓትን ለማስወገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት አስተያየት ሰጪው መንግስት የቸገረውን ይጠይቀን፤ ያማክረን ህይወታችን ሁሉ ለአገራችን እንሰጣለን ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
መቀሌ የመሸገውን ይህን ካህዲ ቡድን ነካክቶ መተው ሳይሆን መንግስት ካሉበት ይዞ ለህግ ማቅረብ እንደማገባ አመልክተዋል።
የህወሓት ቡድን ለሃገርና ህዝብ የማይጨነቅና ሁል ጊዜም ለጥፋት የቆመ ሃይል ነው ያሉት ደግሞ የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አዲሴ መኮንን ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክና ጀግንነትም በተግባር መደገም እንደሚያስፈልግ ገልጸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ወጣቱን አስተባብረው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው ትግል ወንድም በሆነው ሠላማዊው የትግራይ ህዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪ አቶ ፍቃዱ ብሩ እንዳሉት በትግራይ መሽጎ የቆየው የፀረ ሠላም ቡድን በጀግናው መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ግልፅ የሃገር ክህደት ነው።
መንግስት በፀረ ሠላም ሃይሉ ላይ የሚወስደውን የማያዳግም እርምጃ ለትግራይ ህዝብ ጭምር ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ተጓዳኝ እንድሪስ በበኩላቸው የህወሓትን አመራሮች ለረጅም ዓመታት ከኢትዮጰያ ህዝቦች ጀርባ ታዝሎ የኖረ ቡድን ነው ብለዋል።
"ደም እየተራመድን መኖር ይብቃን "ያሉት ወይዘሮ ተጓዳኝ ሰብአዊነት በማይሰማቸው አረመኔዎቹ የህወሓት መሪዎች ላይ መንግስት የጀመረውን እርምጃ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
እራሱን ህወሓት ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ሃይል ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ባለመሆኑ የተጀመረው የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ደግሞ መምህር ተክለ ፃደቅ ይልማ ናቸው።
የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ከሰሞኑ በአካባቢው ባለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን መንግስት በወቅቱ ገልጿል።