የህወሓትን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ የተጀመረውን ጥረት ህብረተሰቡ ሊደግፍ ይገባል--የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓትን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ የተጀመረውን ጥረት ህብረተሰቡ ሊደግፍ ይገባል--የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
አሶሳ ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ እኩይ ተግባሩን ለማጋለጥ ለተጀመረውን ጥረት ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
ጽህፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሚመሩ ፓርቲ እና መንግስት “አጋር” በሚል ስያሜ በሃገራዊ ጉዳዮች ባይተዋር ሆነው መቆየታቸውን አውስቷል፡፡
ይህም በክልል ህዝብ እና መንግስት ላይ ትልቅ የስነ-ልቦና ጫና ማድረሱን ያመለከተው መግለጫው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ጉዳዩ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል ብሏል፡፡
የክልሉ መንግስት እና ፓርቲ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በባለቤትነት መሳተፉ እንቅልፍ የሚነሳቸው አካላት ሴራ በአሁኑ ሰዓት ከሽፏል ሲል ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል፡፡
እንደ መግለጫው የህወሓት ከሃዲ ቡድን “እኛ ካልመራን ሀገር ትፍረስ” በሚል ከንቱ ምኞት አኩርፎ መቀሌ በመመሸግ በተላላኪዎቹ አማካኝነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ፀጥታ በተለያየ መንገድ ሲያውክ እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመተከል ዞን እየተስተዋለ ያለው የፀጥታ መደፍረስ ችግር የቡድኑ እኩይ ተግባር አንዱ ማሳያም እንደሆነ ጠቅሷል፡፡
ህወሓት በክልሉ ብቻ ሳይሆን በመላው ሃገሪቱ ዜጎችን በማፈን፣ በማሰር፣ በማንገላታት እና ጫና በማሳደር ለመምራት የነበረው ቅዠት በለውጥ ኃይሉ መክሸፉ ተስፋ እንዳስቆረጠው ተመልክቷል፡፡
የህወሓት ያለፈ ጸያፍ ድርጊት ሳያንስ ከአብራኩ በወጣው ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ የከፈተው ጥቃት የሚወገዝና እጅግ አስነዋሪ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል፡፡
ድርጊቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ በእጅጉ እንደሚያወግዘው የገለጸው መግለጫው በኢትዮጵያ ታሪክ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ እንደሆነ አስታውቋል።
ዜጎች በሃገራቸው በየትኛውም አካባቢ በህጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው የመኖር፣ እና የመስራት ሙሉ መብት እንዳላቸው በህገ-መንግስቱ እንደተረጋገጠ ያስታወሰው መግለጫው ህወሓትና ተላላኪዎቹ ይህንን በመጻረርና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪዎች እርስ በእርስ በማጋጨት በጥርጣሬ እንዲተያዩ ማድረጉን መግለጫው አውስቷል።
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ እሴቶችን የሚጋሩ በደም የተሳሰሩ ፣በፀረ-ጭቆና ትግልመስዋዕትነት በመክፈል አሁን ላለው የሀገረ መንግስት ምስረታ ጉልህ አሻራ እንዳሳረፉ ተመልክቷል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓትን ከትግራይ ወገኖች ነጥሎ እኩይ ተግባሩን በማጋለጥ በህዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ለማስቀጠል የተጀመረው ጥረት ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር የፓርቲው ጽህፈት ቤት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከትግራይ ህዝብ ጎን በመቆም ህወሓትን በጋራ አሸቀንጥሮ ለመጣል በሚደረገው ጥረት የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡